Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Breaking News, Breaking News Amharic, Ethiopian

Published Posted on by | By TZTA Newsቃለ መጠይቅ

ሜይ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. People to People Canada (P2P) and Cuso International ሲስተር ጥበበ ማኮ Director of Hiwot Integrated Development Association (HIDA) መሥራች፣ ከኢትዮጵያ በመጋበዝ በግሮስቬን በሚገኘው ሴንትራል YMCA አዳራሽ ጠቅለል ባል ሁኔታ ንግግር አድርገው ነበር። ስለ ድርጅታቸው ታሪካዊ አመጣጥ፣ እንዴት ኢትዮጵያውያንን፣ ሕጻናት ተጎጂዎችን እንደረዱ፣ በተጨማሪ በሥራቸው ከአፍሪካና ከአለም አቀፍ ታዋቂ ድርጅቶች ሽልማት እንዳገኙ እለት በእለት ሥራቸው ማስረጃን በማቅረብ ለቤቱ አስረድተዋል። እንግዶችና እንዲሁም የካናዳ ፓርላማ ተወካይ ክቡር ጂም ክራዚያኒ ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል፤ እርሳቸውም ንግግር አድርገዋል። በየተራም የCuso International እና (P2P) ተወካዮችም እንኳን ደህና መጡ በማለት አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል። ለእንግዶች ለስላሳና የሻይ ግብዣም ተደርጓል። የሚገርመው የቀረበው ቁርስ በአገር ባህል ደንብ የተሰራ ልዩ ልዩ ኩኪ መሰል ጣፋጭም ነበር። ከዚያም በአሉ ተፈጽሟል። 

ስለ ሲስተር ጥበበ በይበልጥ ላንባብያን ለማስተዋወቅ የትዝታ ጋዜጣ አዘጋጅ ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል። የትዝታ ጋዜጣም ይህን እድል ስላገኘ ምስጋን ያቀርባል። ስለሆነም በቀጥታ ወደ ቃለ መጠይቁ እንገባለን።

ትዝታ፦                                                                                                                                             እስኪ ሰለራስዎ ለአንባብያን ቢያስተዋው

ሲስተ ርጥበበ፦    
እኔ ስሜ ጥበበ ማኮ ይባላል። የተወለድኩት አዲስ አበባ በዘውዲቱ ሆስፒታል ነበር። ያደጉት ግን አርሲ ክፍለ ሃገር ውስጥ ስሬ በምትባል ትንሽ የገጠር ከተማ ነበር። ያደጉት ከአያቴ ጋር ሲሆን እዚያ በምማርበት ጊዜ አራተኛ ክፍል እያለሁኝ ትልቁ የእናቴና አባቴ ልጅ ውንድሜ በመኪና አደጋ ምክንያት ከወገቡ በታች በድን ሆነ። በወቅቱ እሱን ለመርዳት በተሰቦቼ ወደ አዲስ አበባ ተዘዋወሩ። ትምህርት ቤት ለክረምት ሲዘጋ እኔም ወደ አዲስ አበባ ወንድሜን ለማየት ሄጄ ነበር። ውንድሜንም ሳየው በጣም አዝን ነበር።

ትዝ የሚለኝ ለወደፊቱ ምን ለመሆን ምኞታችሁን ብሎ መምህራችን ድርሰት ጻፉ ስንባል፣ እኔ ምኞቴ የነበረው በድርሰትም እጽፍ የነበርው ሳድግ ሃኪም ለመሆን ነበር። ወንድሜ ገንዘብ እንኳን ባይኖረኝ፡ በእውቀቴ በሙያዬ እረደዋለሁ እል ነበር። እንግዲህ አራተኛ ክፍል ማለት ዕድሜዬ የ10ና ይ11 ዓመት ልጅ ነበር። በዚያ እድሜ የምመኘው ነበር። እና በተፈጥሮዬ ለሰው በጣም አዝናለሁ። ድሮ ሰው ሞቶ ወይም ታሞ በስትሬቸር ሲወሰድ አለቅስ ነበረ እና በአልቃሽነቴ በጣም እታወቃለሁ።

ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በወጣትነቴ ጊዜ ወደ ነርስ ትምህርት ቤት ስገባ ምኞቴ ወንድሜን በቅርቡ ሆኘ በጣም ለመርዳት ነበር። ወደ ዩንቨርስቲ ያልገባሁት እከምጨርስ ድረስ ወንድሜን ሳልረዳው ይሞትብኛል ብዬ በጣም በማዘኔና በማሰቤ ነበር። በወቅጡ ጎበዝና በጣም ጥሩ ተማሪ ነበርኩ። ስለሆነም ነርስ ትምህርት ቤት ገብቼ ወንድሜ እስከ እለተ ሞቱ ለ15 ዓመት የምችለውን ያህል እርዳታ አድርጌአለሁ። የአልጋ ቁስል እንዳያወጣ፣ ሳይሰቃይ ሲሞትም በእጄ ነበር የሞተው። እርሱም እራሱን ችሎ ለረጅም ጊዜ ይሰራ ነበር። እግዛብሔር በምፈልገው መንገድ እንደተመኘሁት አድርጎልኛል።

ቤተሰቦቼ ብዙውን ጊዜ እንዳገባ ይገፋፉኝ ነበር፣ የኔ ምክንያትና ዓላማዬ ወንድሜን ለመርዳት ነበር ነርስ የሆንኩት። አግቢ እያሉም ሲጫኑኝ እኔ አላገባም እል ነበር። እኔ ነርስ የሆንኩት ወንድሜን ለመርዳት ነው፣ ካገባሁኝ ለልጆቼ ነው፣ ካገባሁኝ ለባሌ ነው እንጂ ለውንድሜ አይደለም። ይህ ለእኔ የእግዛብሔር አሥራት ነው፣ ተውኝ እላቸው ነበር። ስለዚህ ቤተሰቦቼ በጣም ያዝኑብኝ ነበር። ይህንን ስለአሰብኩ ወንድሜን እስከመጨረሻ ረድቸዋለሁ።

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ በደርግ በተቀጣችበት ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ በየገጠሩ እየዞርኩ በተለይ (Save the Children Norway) ሴቭ ዘችልድረን ኖርዌይ በሚለው ድርጅት ተሠማርቼ በጣም ብዙ ሕፃናት በረሃብ ምክንያት ሲሞቱ የምችለውን ነገር ሁሉ አድርጌ ነበር። ከሴቭ ሲክ ችልድረን (Save Sick Chilldren) ጋር ሥሰራ ደግሞ እኔ በፊትም ለሰው አዝናለሁ። እንደገና ደግሞ ኖሬጅያኖች በጣም ገጠር ውስጥ ገብተው መሬት ላይ እየተኙ፣ ምግብ ሳይስማማቸው ሲቀር ሲታመሙ ሁልግዜ የኛን ሕዝብ ሲረዱ፤ እኔ ማን ነኝ? የእኔ ወገን አይደለም ወይ? ሳይማር ያስተማረኝ ሕዝብ አይደለም! እኔ ነኝ ኢትዮጵይዊ ወይስ እነሱ! እል ነበር። አንድ የሕፃናት ሓኪም የሆነ ኖሬጂያን ዶክተር ነበር። በድርጊቱ በጣም ልቤ ውስጥ ይገባና ከዚያ በኋላ ለሌሎች መኖር ጀመርኩ። ከዚያም በጅማ፣ በወሎ፣ በአፋርና እንዲሁም በሱማሌ ክልል በሕክምና ሙያ ብዙ እረድቻለሁ።

ትዝታ፦                                                                                                                                              ሲስተር ጥበበ ማኮ  የHiwot Integrated Development Association (HIDA) መሥራችና የኤዘኬቲቨ ዳይሬተር ነዎት። እስኪ ስለዚህ ድርጅትዎ መቼ፣ እንዴት እንደተቋቋመ ቢገልጹልኝ? ዓላማውና ተግባሩን በአጭሩ ቢያስረዱን?

ሲስተር ጥበበ፦የዛሬ 14 ዓመት ነበር እዚሁ ኖረጂያን ሴቭ ችልድረን ሆኜ ሥሰራ ብዙ በተለይ በአዲስ አበባ ዘነበወርቅ ሆስፒታል ተብሎ የሚጠራው በዚያ የስጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች መድሃኒት ለማግኘት እዚያው እየተቀመጡ ይኖራሉ። ወደዚያ ሆስፒታል የሚመጡት በሽተኞች ከየክፍለሃገሩ በሕመማቸው ምክንያት የተሰደዱ፣ በሴተኛ አዳሪነት የሚተዳደሩ እህቶች፣ ትንንሽ አረቄ ቤቶችም በአካባቢው እየሸጡ የሚኖሩ ነበሩ። በዚያ አካባቢ ስለ ኤች አይ ቪ ኢንፎርሜሽን የላቸውም ሲታመሙ አውጥተው ይጥሏቸዋል። አንድ  ልጅ ካላት ትደብቃለች። ይህንን አይቼ ለብዙ ጊዜ ሪፖርት አደርግላቸው ነብር፣ ድጋፍም እንዲያደርጉ ለሴቭ ሲክ ችልድረን  አመለክትላችሁ ነበር። ነገር ግን የነሱ እርዳታ በኤች አይ ቪ ላይ ፎከስ አያደርጉም። ክሊኒክና ቤት ሌላም ሌላም የመሳሰለውን ይሰራሉ። ስለ ኤች አይ ቪ እርዳታ አይሰጡም ነበር። እንደ ጤና ባለሙያነቴ፣ እንደሴትነቴ ፣ እንደሰበአውነቴ ሃላፊነት ስለአለብኝ እምችለውን ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ይህንን Hiwot Integrated Development Association (HIDA) የሚለውን  ድርጅት አቋቋምኩ።ይህን ድርጅት (HIDA)  ሳቋቋም ከራሴ ካጠራቀምኩት ከቆጠብኩት ወይም ሴቭ ካደርግሁት ገንዘብ በማውጣት ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ቦርድ አቋቋምን ዳይሬክተርና ጀነራል ማኔጀርነት ሕጉ ስለሚያስገድድ መሠረትን። ከቋቋምኩ በኋላ በቤተ ክርስቲያን፣ በእድሮች፣ በቶችና በወጣቶች አካባቢ ትምህርት መስጠት ጀመርኩ። ወጣቶችን በማሰልጠን ሌሎች የታመሙትን በሽተኞች በበጎ ፈቃድ ማስታመም ጀመሩኩ። እነኚህ የሰለጠኑ በጎ አድራጊ ወጣቶች በየጎዳናው ተሰማርተው ቤት ለቤት እየዞሩ እርዳታ ይሰጡ ነበር። በጣም የታመሙ በሽተኞች ሃኪሞችና ነርሶች እነዚህ ሊድኑ ስለማይችሉ ጊዚያችንን አናጠፋለን በማለት ትኩረትም አይሰጧቸውም።  ሲሞቱ እንኳን የሚቀብራቸው የለም። ይሄ ነገር በጣም ስለሚያሳዝነኝ ወጣቶች ካሰለጠንኩ በኋላ በበጎ ፈቃደኝነት ይሰራሉ። ያስታምማሉ፣ ቡና እያፈሉ ጎረቤት ሰብስበው ሥነ ልቦናዊ እርዳታ ያደርጋሉ።


እንዲህ እያደረኩ በፈረንጆች በ2000 ዓ.ም. አፍሪካ ዲቨሎፕመንት የሚል ትልቅ ስብሰባ ነበር። ከካናዳ ከአሜሪካ ከሲውድን ከመሳሰሉ የመጡ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ተወላጆች ነበሩ። ስብሰባውም የሚካሀደው ቢ.ሲ.ኤ ነበር። በወቅቱ ብዙ እኔ አልታወቅም ነበርና ማንም ሳይጠራኝ ለመሳተፍ ወደዚሁ ስብሰባ ሄጄ ነበር። በወቅቱ ብዙ ሪፖርቶችና ሪሰርቾች ይቀርቡ ነበር። ታች ብዙ ሰው እየሞተ ነው። የሚቀርበው ሪፖርት ግን በጣም የሚስብ አትራክቲቭ ነበረ። በወቅቱ ለሻይ በሚወጣበት ጊዜ አበሾች ተሳታፊዎች ስለነበሩ ጠጋ ብዬ አናገርኳቸው። የቀረበው ሪፖርት ለመሆኑ እታች ያለው እንደዚህ ይመስላችኋል? አንዱ እንዲህ ብሎ ጠየቀኝ! አንቺ ትሰራለሽ ብሎ ጠየቀኝ! አዎን እሰራለሁ። ታሳይናለሽ? በጣም ደስ ይለኛል። በአጋጣሚ የጠየቀኝ ኢትዮጵያዊ አሜሪካን አገር የሚኖር ነበር። እኔም ወሰድኳቸው። በሚድርሱበት ጊዜ ቤቱ አያስገባም። አጎንብሳችሁ ነው የምትገቡት፣ ከላይም ያፈሳል አልኳቸው። በቤቱ ውስጥ የተኙት በሰውነታቸው ላይ ሥጋ የላቸውም፣ አጥንትና ቆዳ ብቻ፣ አይናቸው የፈጠጠ ነበር። ሰው የሚናፍቁ ነበሩ። ስለዚህ ገብተው ሲይዋቸው በጣም በመገረም ብር ሰጥተውኝ በጣም በተቻለኝ መጠን እኛ እንረዳሻለን አሉኝ። እኔም በጣም ደስ አለኝ።

በወቅቱ ምንም ፈንድ የለኝም። ያቺው የኔው ገንዘብ ነው ያለችው። እሷንም ለእነሱ እንዲሰጥ ነው ያደርኩት። የማገለግለው በነጻ ነበረ። ስለሆነም በወቅቱ ሲጎበኙ በስሜት ተረብሸው ነበር ይመስለኛል አንድ የሽልማት ውድደር ነበር። እርሱም ሃንገር ፕሮጀክት (Hunger Project) እየተባለ ግምገማ ያካሂድ ነበር። ሃንገር ፕሮጀችት ድሮ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የተቋቋመ ትልቅ ኢንተርናሽናል ድርጅት ነበር። ዓላማው ርሃብን ለመዋጋትና የአመራር ብቃት ላሳዩ ሰዎች ሽልማት መስጠት ነበር። በዚህ ሽልማት የደቡብ አፍሪካው ማንዴላና የታንዛናዊ መሪ ተሸልመዋል። መሪዎች ብቻ ነበር የሚሸለሙት።

በ2001 ላይ ግራስ ሩት ላይ የሚሰሩትን ርሃብን ለመዋጋት የአመመራ ብቃት ላሳዩ ሰዎች ሽልማት ስለነበር እኔም ውድድሩ ውስጥ ገባሁኝ። ይመስለኛል እነዚህ የጎበኙኝ ሰዎች ስለመጡ በራሳቸው መንገድ ገምግመው ነበር እኔን ለሽልማቱ የጠቆሙኝ። በወቅቱ ገምጋሚው የሚጠራው Africa Leadership Rise ነበር። ከአፍሪካ አገሮች አራት ተሸላሚዎች ሲመረጡ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዝምባብዌ እንዲሁም ሩዋንዳ ነበሩ። በአሸናፊነት እኔ ስለወጣሁ $54 ሺህ ዶላር ሽልማት ተሰጠኝ። እኔም በጣም አለቀስኩ። በወቅቱ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አብዱል መጅድ ነበሩ። ታዲያ ያገኘሁትን ሽልማት አሥር ሳንቲም እንኳን ሳልነካ ለድርጅቴ አበርክቻለሁ። ይህ ሽልማት ያገኘሁት የኔ ጥረት ሳይሆን በነጻ እናት አባት የጠላውን ጠርገው፣ ተቅማጡን አጽድተው በነጻ በበጎ ፈቃድ ሕጻናትን የሚያገለግሉ ውጤት ስለነበር ነው። ይህ የተገኘው ገንዝብ አዲስ ፕሮግራም በመክፈት በመላው አስርቱ ክፍለ ከተማ የበጎ ፈቃደኞችን እየጨመረ ሥልጠና እየተደርገላቸው የታመሙ ሰዎችን መርዳት ተጀመረ። አንድ ትዝ የሚለኝ CRDA እባካችሁን አባል አድርጉኝ ብዬ ስጠይቃቸው አቅም የለሽም ብለው ተውኝ። እኔ ግን ለማሸነፍ በቃሁ።

ከአመት በኋላ ፈንድ እየጨመረ መጣ። የአሜሪካ ፓክት ኮሚኒቲ ሉት የሚባል ዋሽንግተን ውስጥ ነበር። በዚህም ተወዳድሬ የ150 ሺህ ዶላር ፕሮጀችት አገኘሁኝ። ከዚያም ሎሬት የሚል ማእረግም አገኘሁ። እየቀጠልንም ፈንድ ማግኘት ተጀመረ። ከዚያ በኋላ 45 ሺህ የሚሆኑ የታመሙ ሰዎችን መርዳት ጀመርን። ከዚያም እያደግን መጣን፣ የበጎ ፈቃድ ሰራተኞች እየጨመሩ፣ የሚገርመው ድሆች ናቸው ፣ ነገር ግን እነሱ ሥልጠና እያገኙ። የሥራ እድል ሲኖር ቅድሚያ ለነዚህ በጎ ፈቃድ ሠራተኖች ይሰጣል።

ሌላው ደግሞ ከሰራሁት ሥራ ደስ የሚለኝ በ2003 ዓ.ም. ለሽልማት ውጤት ተዘጋጅቼ በወቅቱ አምባሳደር ፍትጉ የሚባሉ ቦርድ ኦፍ ዳይሬክተር ስብሰባ ሲያደርጉ ንግግር እንዳደርግ በተለይ ስለ ሴቶች ጋብዘውኝ ነበር። እዚያም ቆሜ የዛሬ ኢትዮጵያውያን ደሃ ሴቶች ችግር አለ፣ በኢትዮጲያ ውስጥ ረሃብ አለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጹህ ውሃ አገልግሎት የለም፣ ሴትች ሶስት አራት ሰእት እየተጓዙ ነው ውሃ የሚቀዱት፣ ክልኒክ የላቸውም፣ ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት የላቸውም፣ ገንዘብ የላቸውም እና እኛ እርዳታ እንድትሰጡን አይደለም። እምንፈልገው ሌላ ሃገር የምትሰሩትን የእድገት ሥራ በሃገራችን ላይ እንድታደርጉ በሴቶች ስም እማፀናለሁ። እናንተ ውሳኔ ሰጪዎች ናቸሁ። ስለዚህ ኢትዮጵያ በረሃብ የምትታወቅ ናት ስለዚህ ይህንን የእድገት ሥራ እዚህ እንድትሰሩ እጠይቃለሁ አልኩ።

የነሱ ፕሪንስፕል ኢትዮጵያ አንድ ቢሮ ለመክፈት አንድ ሎሬት መኖር አለበት የሚል ነበር። ሎሬት ደግሞ እኔ አለሁ። እንድ ቦርድ ኦፍ ዳይሬክተር ሆኜ አገለግላለሁ። ይህ የበጎ ሥራ አገልግሎት ነው። አሁን በኢትዮጵያ በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ገጠር ውስጥ የሕጻናት ማሳደጊያ፣ ክሊኒክ፣ የእህል ባንክ ክሬዲት ማህበር፣ ለሴቶች ፋሚሊ ፕላኒግ ፣ በወለጋ መስመር በአምቦ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ፣ መተክል ላይ፣ በጉራጌ እንሞር የተባሉት ቦታ ይገኛል። ሆኖም እኔ ከሰራሁት ቦታ አብዛኛውን ገጥር አካባቢ ለማዳረስ አልቻልኩም ለምን ያለኝ ሪሶርስ የተወሰነ ነበረና። የእነሱ ግን አለማቀፋዊ ነው። እኔም በቦርድ አገለግላለሁ። በተለይ የገጠሪቷን ሴት በመድረሴ ይህ ፕሮጀችት እዚያ በመከፈቱ በጣም እጅግ ያኮራኛል። ልክ እዚያ ባመለከትኩ በአንድ አመት ውስጥ ቢሮ ተከፈተልኝ። አሁን የነገርኳችሁ ሥር ሁሉ ተሠራ።

 ወዲያውኑ ሌላ ሽልማት አግኘሁ። ሴንትራል ኦፍ ኢንተርናሽናል ለርኒግ (Central of International Learning) የሚባለው ድርጅት ሆም ቤዝ ኬር (Home Base Care) በቤት ውስጥ ለበሽተኞች እንክብካቤ መስጠት ከሆስፒታል ውጭ ማለት ነው፣ እዛም እንዲሁ ሽልማት አግኘሁ።

 በ2004 ዓ.ም. የዓለም ኤድስ ኮንፍራንስ ታይላንድ ውስጥ ይካሄድ ነበር። እዚያ የእድሮች ተሳትፎ ባሕልን ያካተተ አሠራር ባለው ተቋማት ላይ የሚሠራ ተብሎ እዚያ ከመቶ አገሮች ተወዳድሬ ሽልማት አገኘሁ። የተሸለሙ አገሮች፣ ኢትዮጵያ፣ ኮምቦዲያ፣ ሩዋንዳ ፣ ሕንድ አንድ አራት አገሮች ነበሩ። ከኢትዮጵያ የተሸለመው የኔ ድርጅት ነው። ይህ እንግዲህ በአለም አቀፍ ደረጃ ነው።

ሌላው ደግሞ ወርልድ ኦፍ ችልድረን (World of Children) የተባለ የኖብል ሽልማት፣ ለሕፃናት $15 ሺህ ተሰጠን። እንዲህ እያለ ድርጅታችን ዕውቅና አግኝቷል።

ትዝታ፦                                                                                                                                            ድርጅትዎ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሥራዎችዎን ለመተግበር ምን መንገድ ወይም ፕሮግራም ተጠቀሙ?

ሲስተ ጥበበ፦ 
የድርጅታችንን ዓላማ ለመተግበር አራት የፕሮግራም መንገዶች አሉን።                                                                           1ኛ/ የሕፃን አገልግሎት በተለይ ወላጆቻችውን ላጡ ሕፃናት፣ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት፣ የድሃ ልጆች በትምህርት፣ በጤና፣ በቤተሰብ የገቢ ማስገኛ፣ በሕፃናት ላይ የጉልበት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከለላ መስጠት፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት…ወዘተ ይሆናል።
2ኛ/ ኮሚኒቲ ቤዝድ የሆነ የጤና አገልግሎት መስጠት። አንዱም ኤ.ች.አይ.ቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትምህርት መስጠት። ለቤተሰብ ሁለተኛ ነገር ደግሞ የታመሙ ሰዎች እንክብካቤ ማድረግና በተለይ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ፣ በፋሚሊ ፕላኒግ፣ በሰብ ተዋልዶ ጤና፣ ቫይረሱ ደግሞ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ጤናማ ሕጻን እንዲሆን፣ አንድም ልጅ ከኤች አይ ቪ ጋር መወለድ የለበትም በሚል መርህ በነዚህ ሥራ መሥራት ነው።                                                                                                                   3ኛ/ ለገቢ ማስገኛ መስራት፣ ሰዎች ሁልጊዜ በእርዳታ መኖር የለባቸውም። አቅማቸው በሚፈቅደው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ መስጠት ነው።  አራት ዓይነት የብድር አሰጣጥ አለ። ሀ)የብድር አገልግሎት ለ)እነሱ ቆጥበው ከቆጠቡት ሌላ ተጨማሪ መስጠት ሐ)የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ። እኮነሚያቸው በዳበረ ቁጥር እነሱም ለህሊናቸው ከተረጅነት ይወጣሉ ማለት ነው። ሠ) የአቅም ግንባታ እድል።
 4ኛ/ከቀብር ባሻገር ልማት እንዲሰሩ እየሰሩም ነው።  እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ ሥልጠና መስጠት፤ በሊደርሺፕም ስልጠና ይሰጣል። በየአካባቢያቸው ገንዘብ እያዋጡ መንገድ እየሰሩ መብራት እያስገቡ ነው። ስለዚህ ዕድር መቅበር ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸን እንዲያለሙ እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ ማድረግ ነውና! ዋና ዋና ትግባሮች እነዚህ ናቸው።

ትዝታ፦ ዋና ዋን ያጋጠመዎት ችግር ካለ? ምንስ እርምጃ ወሰዱ?

ሲስተር ጥበበ፦                                                                                                                          በመጀመሪያ የጋጠመኝ ትልቁ ችግር ያመለካክት ለውጥ አለማድረግ ነው። ሰው ተረጂ ወይም መጎዳት ብቻ እንጂ መሥራት አይፈልግም። እርዳታ ብቻ ነው የሚፈልገው። ይህ አንዱ ከፍተኛ ችግራችን ነው።

 ሁለተኛ ደግሞ የሪሶርስ አለመመጣጠን ነው። የድሃው ብዛት የሪሶርስ እጥረትና አለም አቀፋዊ ክራይሥስ አንዱ ሌላው ትልቁ ችግራችን ነው።

ሦስተኛ ስለ ቢሮ ጉዳይ ስናወሳ ከመንግሥት አለመተባበር አለ። አሁን እኛ መንግሥት ለቀየሰው ዓላማ ድህነትን ለመቀነስ፣ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር ነው። ለዚህ ግን ለግለሰብ ቤት ኪራይ እየከፈልን ነው ያለነው፣ ቢሮ ለመስራት መሬት በሊዝ እንደ ነጋዴና ኢንቬስተር  በቅድሚያ ለእኛ አይሰጥም ይህ የሁላችን ችግር ነው። ከአሁን ቀደም ለሕፃናት ፈንድ ተገኝቶ መሬት ለማግኘት በጣም ተቸገርን፣ ስለሆነም ፈንዱ ሊመለስብን ነው። ይህ አንደኛው ታላቅ ቻሌንጃችን ነው። መሬት ካላገኘን ፈንድ ሰጭዎቹ በምንም አኳዃን ገንዘቡ ሊከፈሉን አይችሉም። ይህ የአገሪቱ በረከት መሆን ያለበት ነው እንጂ እንደገና መሬት ገዝቶ ለነጋዴ ኢንቬስተር ለዚህ ግን አይሰጥም ይህ ትልቁ ችግራችን ነው።

ትዝታ፦                                                                                                                                      በህይወትዎ እስከዛሬ የሚያደንቁት ነገር ካለ?

ሲስተር ጥበበ፦                                                                                                                            ይህን ሥራ ከመጀመሬ በፊት የማስታውሳቸው አንድ ታላቅ ሴትዮ አሉ። እኝህ ሴትዮ ሳይማሩ የተከበሩ ኢትዮጵያዊ የቤት እመቤት ወይዘሮ አበበች ጎበና ናቸው። እኝህ እመቤት ግሼን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊሳለሙ የዛሬ 30 ዓመት ይሆናል ሄደው ነበር። ተሳልመው ሲመጡ በረሃብ ምክንያት እናቱ ሞታ ልጁን ያያሉ፣ በጣም አዝነው ልጁን ይዘው ወደ ቤታቸው ይሄዳል። ከዚያ በኋላ ልጆችን ስብስበው ቤታቸው ውስጥ ማሳደግ ይጀምራሉ። በዚያም ምክንያት ትዳራቸውን ሁሉ አጥተዋል; ለምን ልጆች ትሰበስቢያለሽ በማለት ባለቤታቸው ትተዋቸው ሄድዋል። እኚህ ሴትዮ ዛሬ ለብዙዎቻችን ኢንስፓየርድ ያደርጉ ትልቅ ሮል ሞዴል የሆኑ ናቸው። አሁን በየክልሉ ብዙ ትምህርት ቤት አሰርትዋል፣ ሴቶች በራሳቸው ገቢ እያገኙ ነው፣ የሳቸው ልጆች ከዩኒቨርስቲ ጨርሰው በተለያዩ ስራዎች ተመድበው አስተዋጾ እያደረጉ ይገኛሉ። አሁን እሳቸው በሕይወታቸው ቢድክማቸውም ውጤታቸውን እያዩ ነው። ስራው በሚገባ አሁንም እየተካሄደ ነው። እንግዲህ እርሳቸው እንዲህ ካደረጉ እኛስ ለምን ሃላፊነት የለንም። አንድ ቀን የርሳቸውን አርማ አናነሳም ወይ? እኔ ማርትሬዛን በጣም አደንቃለሁ። ነገር ግን የአገሬ ሰው እንደ ወይዘሮ አበበች ጎበና የበለጠ የማደንቃቸው እንስፓየር ያደረጉኝ ሴት ናቸው። እኔም በጣም ደስ ይለኛል።

ደስ የሚልሽ ነገር እንዳልከኝ፤ ሁሉ ከኔጋ ይሰሩ የነበሩ፣ ከኔጋ እየወጡ እኔ እንደ ሮል ሞዴል ይዘው በራሳቸው ተመሳሳይ ሥራ የጀመሩ ሴቶች አሉ። እኔጋ ይሠሩ ስለነበረ ስለዚህ ያስደስተኛል። እኔ ሁሉ ጋ ልደርስ አልችልም። ይህ ንግድ አይደለም። የበጎ አድራጎት ሥራ ነው። የኔን ዓርማ ሌላው ሰው ሲያነሳ ይሄነው በጣም የሚያስደስተኝ።  ምንም የሂሊና ወቀሳ የለብኝም፣ ድርሻዬን ተወጥቻለሁ።

ትዝታ፦                                                                                                                                                         አሁን በካናዳ የሚገኙት People to People Canada (P2P)  እና  Cuso International   ከርስዎ ድርጅት ጋር ሊገናኝ ቻለ።

ሲስተር ጥበበ፦
በኢትዮጵያ ውስጥ እነኚህ ሁለት ድርጅቶች የየራሳቸው ፕርግራምና ቢሮ አላቸው። በዓለም አቀፍ በጎ ፈቃደኞች አንዱ የሆነው Cuso International በካናዳ ሲሆን  ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮግራም አለው። ስለሆነም ወደ እኔ ጋ ከአንድ ሦስት ጊዜ መጥተው ከፍተኛ አስተዋፆ እና እርዳታ አድርገዋል። ፈንድ ሬዚንግ የሚያደርጉ፣ ፕሮፖዛል የሚጽፉ፣ አንድ አንድ ሙያዊ ስኪል የሚሰጡ ሲሆኑ የነዚሁን ወጪ የሚሸፍነው ኩሶ ኢንተርናሺናል ነው። እኛ ሆም ኬር አለን። የቮለንትየር ፖሊሲ አለን፣ ዲቬሎፕ ስናደርግ ለዚህ እርዳታ የሰጠን ኩሶ ኢንተርናሽናል ነው። ሥልጠናውን በዲፕሎም አድርገናል፤  ለዚህም የሸፈነልን ኩሶ ኢንተርናሽናል ነው። የካፓሲቲ ሥራ ስልጠና ለበጎ ፈቃድኞች ይሰጣሉ። በጣም የሚደንቀው ግልጽነት፣ እኩልነት፣ የበላይና የበታች የሌለበት ስለሆነ ይህ ለፓርትነርሽፕ ከፍተኛ ጥንካሬ ይኖረዋል። እኛም ከነሱ እነሱ ከኛ እንማማራለን። አምስት አመት ፕላን ስትርተጂክ ፕላን ሲስሩ ለእኛ ተገቢ እርዳታ አድርገዋል። እኛም ኮሜንት እንድናደርግ አድርገዋል። ሚሽናችንንም ሼር እድርገናል። እኛ ጤና፣ ትምህርትና ገቢ ማስገኛ ላይ እንሰራለን እነሱም እንደዚያው ቪዥናችን ተመሳሳይ ነው። ለአንድ ዓላማ አንድ ጎል ገብ ላይ ነን።

ፒቱፒ ቀደም ብሎ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ለረዥም ጊዜ አብረን የተጓዝነው፡ ልጆች ስፖንሰር ሺፕ ያደርጋሉ። ሕፃናት ማቆያ ፈንድ የተደረገው ከፒ ቱ ፒ ነው። ሌላው ትልቁ ኳሊታቸው ከሌላ የሚለዩት ክትትላቸው ነው፣ ብር ስጥተው ዝም ማለት ሳይሆን፣ ገንዘቡ ለምን እንደዋለ፣ ልጆቹ ቤት ድረስ እየሄዱ እንዴት ናቸው። ስጦታ ስጥተው፣ አብረዋቸው ምሣ ብልተው፣ ክሪስመስ ፓርቲ እንደማንኛውም አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ፣ በሙዚቃ በቪዲዮ ግራፈር እንዲሰለጥኑ፣ ወጣቱ አቅሙ እንዲጎለብት ይህንን ሁሉ በፒ ቱ ፒ ስፖንሰር ተደርገዋል። ስለዚህ ከአንድ ዜጋ እርዳታ ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። በክሪስመስ ፓርቲ ላይ ምሣ ሰርቭ የሚያደርጉ እነሱ ናቸው። መጥተው ትልቅ ስብሰባ ወስጥ ይገኛሉ።ሪፖርት በውቅቱ እናደርጋለን፣ በየጊዜው ኦዲት የተደርገውን ስፖንሰር ያገኙታል። ይህ በእውነቱ ለሌላው ምሳሌ ይሆናል።

ትዝታ፤-                                                                                                                             ከኢትዮጵያ መንግሥት የምታገኙት እርዳታ አላችሁን?

ሲስተር ጥበበ፦
ከኢትዮጵያ መንግሥት ምንም እርዳታ አናገኝም። በእርግጥ ጥሩ የሆነ ግንኙነት አለን። እኔ እታች በቀበሌ ደረጃ በኦፊስ ደረጃ የምሰራ ነኝ። በእርግጥ አንድ ነገር መንግሥት ባይፈቅድ ሥራ አንሠራም። አግሪመንት ተደርጎ ፈቃዱ ስለአለን በኛ ላይ እምነት አላቸው። እኛም ሃላፊነታችን አውቀን ከተፈቀደልን ሥራ ውጭ ወደ ሌላ እጃችንን እንደማናስገብ ይታወቃል። በተረፈ ቻሌንጆች አሉ ቤት ለመስራት ቦታ ማጣት ሲሆን፣ በተረፈ ድጋፍ ደብዳቤ ጻፉልን ስንል ይጽፉልናል። ሪኮሜንድ አድርጉልን ስንላቸው ይተባብሩናል። እያንዳንዳችን ግልጽ ነን; የምንደብቀው ነገር የለም፤ ሁሉንም መንግሥት ያውቀዋል። በየእመቱ በኢክስተርናል ኤክስፐርት ኦደት ተደርጎ ሪፖርት ይቀርባል። በየኳርተሩም ጭምር። ይህንን ነገር እንዲያውቁ ጥሩ ግንኙነት አለን።

ትዝታ፦                                                                                                                                                  እስከ ዛሬ አምስት አምት ድርጅትዎ የት ይደርሳል ብለው ያስባል?

ሲስተር ጥበበ፦
ቅድም እንደገለጽኩት ሁሉ በየክልሉ ይህንን የያዝነውን በፕሮግራም እንዲዳረስ ማደረግ ነው። እኔ አንድ ነገር ብሆን ድርጅቱ ራሱን ችሎ ይቀጥላል።

ትዝታ፦ 
ካላይ ያልጠቀስኩት ለአንባቢያን ይሚሉት ነገር ካለ?

ሲስተር ጥበበ፦
እኔ በተለይ ይህንን ኢንተርቪው የሚደርሳቸው በመላው ኢትዮጵያና ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ምክንያት ከሃገር የወጡ፣ ነገር ግን ልባቸው አገራቸው ውስጥ ያለ፣ እትብታቸው የተቀበርችባት ያቺ ሃገር፣ ያቺ ደሃዋ፣ ያቺ ምስኪኗ፣ ሕፃናት የሚራቡባት፣ ዛሬም በትምህርት የማይሄዱባት፣ ዛሬም ችግር በችግር አሮንቃ ውስጥ ያለችው እና ሃላፊነታችንን እንወጣ፣ እንርዳ፣ እኛ ያልደረስንላቸው ማን ይደርስላቸዋል? ከኛ የቀረበ ማንም የላቸውም፣ ሳይማር ያስተማረን ሕዝብ ጠቀምነው ማለት ነው? ግደታችንን ሃላፊነታችንን ተወጣን ማለት ነው? ስለዚህ በቶሮንቶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኦርጋናይዝድ የሆነ ድርጅት አለን፣ ፒ ቱ ፒ በበጎ ፈቃደኞች ሰራ በመሳተፍ፣ ለሕፃናትን አገልግሎት ለመስጠት በተለያየ ምክንያት መደጋገፍ ይገባል፣ አብረን እንበላለን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ በሃዝን በችግር አብረን ነው ያለነው፣ ግን በሃገር ላይ በሕፃናት ላይ አለኝታ ማለት ሕዝብ ነው። ይህንን ነገር በአንድነት ሆነን ሕጻናትን እንደግፋቸው። ይኸም ለራሳችን ሴኩሪት ስንል ነው። ዛሬ ያልረዳነው ልጅ ዛሬ ያልሰጠነው ልጅ ዛሬ አይዞህ ያላልነው ልጅ ነገ የአገር ጠንቅ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይሄ ሁሉ ሃላፊነት ለውጭ አገር ሰዎች ሳይሆን የራሳችን ሃላፊነት ሲሆን  አብረን እንሰራ። መርዳት የምትፈልጉ በቀጥታ መርዳት ይቻላል ወይም በፒ ቱ ፒ በካናዳ ሕጋዊ ይሆነ ድርጅት ነው በዚያ በኩል መርዳት ይቻላል። 

ይህንን እድል ስለሰጡኝ እጅግ በጣም አምሰግናልሁ።እግዚአብሄር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ እላለሁ።

እርሶም ስለተባበሩን በጣም አድርገን እናመሰግናለን። ትዝታ                       


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu