Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Breaking News Amharic, Ethiopian

በአገራችንና ህዝቧ ላይ ያንዣበበውን አደጋ አስወግደን የጋራ አገር ለመገንባት እንረባረብ

Published Posted on by | By TZTA News
Spread the love

ከኢትዮጵያዊያን ተጋሩ የውይይት መድረክ
ጥር 2010 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 2018)

(**ውድ ኢትዮጵያዊያን ይህንን መግለጫ ለማውጣት ጽፈን ከጨረስን በኃላ ወደ
ሚድያዎች ለማሰራጨት ስንዘጋጅ የወልድያና አካብቢው በጥምቀት ቀን ለደረሰው
የወንድሞቻችን እልቂት በጣም አሳዝኖናል:: ለመላው ቤተሰብ መፅናናትን አንመኛለን)
በህወሓት መሪነት ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ስልጣን የጨበጠው ኢህአዴግ የጋራ
ማንነታችን በሆነው ኢትዮጵያዊነት ላይ በህግ አስደግፎ ስለዘመተ ዛሬ ኢትዮጵያዊነት
በብዙዎች ዘንድ ደብዝዞ በየብሄራቸው/ብሄረሰባቸው ማንነታቸው የሚታበዩና
ከብሄራቸው/ብሄረሰባቸው ውጭ የሆኑትን የሌላ ብሄር/ብሄረሰብ ተወላጆችን በጥላቻ ዓይን
የሚያዩና በብሄር/ብሄረስብ ላይ ያተኮረ ጥላቻ የሚሰብኩ፣ ጭካኔ የተሞላበት ግዲያና
ማፈናቀል ድረስ የሚሄዱ ዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መሆናቸው በግልጽ እያየን
ነው። ባሳለፍናቸው 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን አደብዝዞ ሁሉም በየብሄሩ/ብሄረሰቡ
እንዲያስብ፣ ከራስ ብሄር/ብሄረሰብ ውጭ የሆነ በጥላቻ ዓይን እንዲያይ በማስደረግና
ከተለያዩ ብሄሮች/ብሄረሰቦች አገዛዙን በተቃወሙ ዜጎች ላይ በተወሰደው የጭካኔ ግድያ፣
እስራትና መፈናቀል የአገዛዙ ቁንጮ የሆነው ህወሓት ድርጊቶቹን በመፈጸምም
በማስፈጸምም ዋናውን ሚና የሚወስድ ሆኖ በተለያዩ ብሄር/ብሄረሰብ አባላት ላይ
የተፈጸሙ ዘግናኝ ግድያዎችን፣ እስራቶችና ማፈናቀሎች በህወሓት ካድሬዎች ትእዛዝ
ሰጭነት የተፈጸሙ ሆነው እነዚህ ካድሬዎች ግፉን ሲፈጽሙ ደግሞ ህወሓት ማለት ህዝቢ
ትግራይ፣ ህዝቢ ትግራይ ማለት ህወሓት ኢዩ (ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ፣
የትግራይ ህዝብ ማለት ደግሞ ህወሓት ማለት ነው) በማለት ይፈጽሙት እንደነበረ ሁሉም
የሚያውቀው ሃቅ ነው።
ይህ የህወሓት መሪዎች የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው እያሉ በትግራይ ህዝብ
ስም እየነገዱ የግል ስልጣናቸውና ጥቅማቸውን የማካበት ቅጥፈት ገና ከጅምሩ ማጋለጥና
መታገል ከነበረባቸው የትግራይ ምሁራን አብዛኛዎቹ በዝምታ ማየቱን ስለመረጡና ከዚህ
የተነሳ የተለያዩ ጽንፈኖች የትግራይ ህዝብን ከህወሓት ጋራ አንድ አድርገው በመሳል፣
የህወሓት ጥፋቶች የትግራይ ህዝብ ጥፋቶች እንደሆኑ አድርገው በማቅረብና ለዚህም
በማስረጃነት የህወሓት መሪዎችና ካድሬዎች የሚሉትንና የሚፈጽሙትን በመጥቀስ ሌላው
ኢትዮጵያዊ የትግራይ ህዝብን በጥርጣሬና በጥላቻ ዓይን እንዲያይ በስፋት ስለዘመቱ ዛሬ
የትግራይ ህዝብን በጥርጣሬና በጥላቻ ዓይን የሚያዩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ተበራክተዋል::
ከ27 ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ ከፋፍለህ – እርስ በርስ እያባላህ – ግዛ አገዛዝ በኋላ ዛሬ
አገራችን ኢትዮጵያ ከምንጊዜም በላይ ህዝቧ እርስ በራሱ ተባልቶ አገሪቷ የመበታተን
አደጋ አንዣብቦባታል። ይህ አሁን በአገራችንና በህዝባችን ያንዣበበው ከባድ አደጋ
የአደጋው ዋና መንስኤ የሆነው አገዛዝ ብቻውንና እሱ በሚፈልገው መንገድ ብቻ ሊፈታው
ከምችልበት ደረጃ ስላለፈ ዛሬ አደጋ ውስጥ ያለችውን የጋራ አገር ለማዳን ሲባል ጉዳዩ
የሚመለከታቸው ዜጎቿን ሁሉ ያለ ቅድመሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ሰፊ የጋራ መድረክ
ፈጥረን ባለጉዳዮች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመክሩ ለማስደረግ ሁሉም የየድርሻውን
እንዲሰራ የግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለሆነም ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ሁላችን
በተቃውሞ ጎራ የቆምን ሆነ በገዢው ፓርቲ በኩል ያሉት ቆም ብለን ልናስብና ከዚህ
ካንዣበበብን አደጋ እንዴት እንውጣ፣ እንዴት በመካከላችን ተፈጥሮ ያለው ቅራኔና ጥላቻ
አስወግደን እርቀ-ሰላም በመካከላችን አውርደን ወደፊት እንቀጥል በሚለው በግልጽና
በስፋት መወያየት/መነጋገር ኣለብን ብለን እናምናለን።
ስለሆንም እኛ በኢትዮጵያዊያን ተጋሩ የውይይት መድረክ ስር የተሰባሰብን ተጋሩ ይህን
አገራችን ከገባችበት ዓዘቅት ለማውጣትና አሁን በተለያዩ ብሄሮች መካከል የተጀመረው
በብሄር ላይ ያተኮረ ጥላቻና የርስ በርስ መገዳደልና መፈናቀል አስቁመን በአገርቷ ላይ
ያንዣበበውን አደጋ ለመቅረፍ ምን ማደረግ አለብን በሚለው ትልቅ ጉዳይ በኢትዮጵያ
አንድነት ጽኑ እምነት አላቸው፣ ተከስቶ ባለው አደጋ እንደኛው ተጨንቀው የጋራ መፍትሄ
በመፈለግ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለን ከጋበዝናቸው ኢትዮጵያዊያን ጋራ በጃንዋሪ 14
2018 በቴለኮንፈረንስ መክረን ከነዚህ ወገኖቻችን በተሰጡን በጎ ሀሳቦች/አስተያየቶች
መሰረት በአገራችንና ህዝቧ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በጋራ አስቀርተን ሁላችን በእኩልነት
የምንኖርባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚከተለውን ጥሪ ለመላው ኢትዮጵያዊያን
እናቀርባለን።
ሀ. ለኢህአዴግ መንግስት፣
አገራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ስንል የፖለቲካ እስረኞችን
እንፈታልን፣ ከደርግ አገዛዝ ጀምሮ ዛሬም የቀጠለው እጅግ ብዙ ዘግናኝ ግፍ
የሚፈጸምበት ማእከላዊ በመባል የሚታወቀውን የሰቆቃ ወህኒ ቤት እንዘጋልን
ማለታችሁ እንደ በጎ ጅምር የሚታይ ሆኖ እውነት የመጠፋፋት ፖለቲካ አቁሞ
ኢህአዴግንም የጨመረ መፍትሄ እንዲመጣ ከልብ ከተፈለገ፣ የፖለቲካ እስረኞች
መፍታት በተመለከተ ሁሉም በአገሪቷ በተለያዩ ክልሎች ያሉ የፖለቲካ እስረኞች
ያለምንም ቅድመሁኔታ ያካተተ መሆን አለበት፣ ማእከላዊ መዝጋት ሲባል ደግሞ በአዲስ
አበባ ያለውን ማእከላዊ ብቻ ሳይሆን በየክልሉ ያሉ ደህንነቶች የተለያየ ሰቆቃ
የሚፈጽሙባቸው የሚታወቁም ድብቅ የሆኑ በርካታ ማእከላዊዎችንም የጨመረ መሆን
አለበት እንላለን።
ሀቀኛ አገራዊ መግባባትና ትክክለኛ የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት እንዲኖር ከልብ ከተፈለገ
ከሁሉ አስቀድማችሁ ኢትዮጵያ ዛሬ የገባችበት ቀውስ በናንተና እናንተ መርጣችሁ
በምታቀርቡዋቸው ድርጅቶች ደረጃ ብቻ ሊፈታ እንደማይችል አምናችሁ ጉዳዩ
የሚመለከታቸው ድርጅቶች በሙሉ ያለ ቅድመሁኔታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት
መሪዎች፣ ምሁራን ያለ ቅድመሁኔታ ያሳተፈ፥ እንዴት ያለውን ችግር በጋራ ፈትተን
ወደፊት እንቀጥል በሚለው የሚመከርበት ሰፊ መድረክ መፍቀድ አለባችሁ እንላለን።
ለ. ለሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ፣
አገራችን ዛሬ ገብታበት ካለችው አጣብቂኝ ለማስወጣት የሚደረግ ትግል በተናጠል
በአንድ ድርጅት ወይም ስብስብ ደረጃ ሊሆን ከምችልበት ደረጃ አልፏል።
ህወሓት/ኢህአዴግ አገራዊ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት አገሪቱ ከገባችበት
አደገኛ ማጥ በግዜ ማውጣት ካልቻለና ለተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ካልሰራ ከምንም
በላይ አገርንና ህዝቧን ከህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በጋራ ተረባርቦ ማዳንና ከወዲሁ በድህረ
ኢህአዴግ አገዛዝ መኖር ስለሚገባት ኢትዮጵያ በጋራ መምከር መጀመር የሁሉም
ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖር መቀጠል አለበት የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ተቀዳሚ
የቤት ስራ ሆኗል። ስለሆነም ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያ
መኖር አለባት የምትሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በመካከላችሁ ያለውን ልዩነት/ቅራኔ
በጋራ በምንመሰርተው ስርዓት እንዲታይ አሳድራችሁ የጥፋት ደመና ያንዣበበባት አገርን
በጋራ ለማዳን አንድ ቅንጅት እንድትፈጥሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ሐ. ለሁሉም የሚዲያ ተቋማት፣
አገራችንና ህዝቧ አሁን ገብተውበት ያለውን ቀውስ በማርገብ ብሎም በመፍታት
በተቃራኒው ደግሞ ተጀምሮ ባለው ቀውስ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ በማቀጣጠል ሚዲያ
ሊጫወተው የሚችለው ሚና ከናንተ የበለጠ የሚያውቅ የለምና በምታስተላልፉት ዜና ሆነ
ሀተታና ትንታኔ ሚዛናዊና በመረጃ ላይ አስደግፋችሁ እንድታስተላልፉ እንማጸናችሁ
አለን። በተለይ መሰረታችሁ በዲያስፖራ ያደረጋችሁ አብዛኛው ሚዲያ የትግራይ ህዝብና
ህወሓት አንድ አድርጋችሁ ስላችሁ የምታቀርቡት እጅግ የተሳሳተና አደገኛ አካሄድ
የትግራይ ህዝብን ብቻ ሳይሆን መላው ሃገርንና ህዝብን የሚጎዳ ስለሆነ ይህን አካሄድ በግዜ
ብታቆሙት የተሻለ ነው እንላለን። ይህ ስንል ግን በህወሓት መሪዎች ፊታውራሪነት
የሚፈጸመው ግፍ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ መቃወምና መታገል የሚገባው የነበረ ግን
ዝምታን መርጦ ያለውን የተወሰነውን የትግራይ ኤሊትን ዝም በሉት ማለታችን
እንዳይደለ ከወዲሁ ልናሳውቃችሁ እንፈልጋለን።
መ. ለትግራይ ምሁራንና ወጣቶች ፣
ላለፉት 27 ዓመታት የትግራይ ህዝብ ከማንም ኢትዮጵያዊ ህዝብ በባሰ ደረጃ በህወሓት
መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ተረግጦ እየተገዛ ያለ ህዝብ መሆኑ ከናንተ ከትግራይ ምሁራንና
ወጣቶች የበለጠ የሚያውቅ ማንም የለም። የአንድ ህዝብ አፍ ሆኖ የሚናገር፣ የሚታገልና
የሚያታግል ምሁሩና ወጣቱ ሆኖ እያለ እስከዛሬ ላለፉት 27 ዓመታት የትግራይ ህዝብ
በህወሓት ተረግጦ ሲገዛና በተለያዩ ጽንፈኞች ያልበላውን በላ፣ ያላለፈለትን አለፈለት፣
የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው ተብሎ ሲሰበክ፣ የህወሓት መሪዎችና
ካድሬዎቻቸው የሚፈጽሙት ወንጀል ለሱ ሲሰጥና በዚህ መሰረትም በሌሎች እንዲጠላ
በጽንፈኞች ጥላቻ ሲሰበክበት አብዛኛዎቹ የትግራይ ምሁራን፥ ሀቁን በማጋለጥ ፈንታ
ለምን ዝምታን መረጡ የሚለው ገና ያልተፈታ እንቆቁልሽ ነው።
ዛሬ በአርቤትና በተለይ በዲያስፖራ የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ተደርገው
እንዲሳሉና ጽንፈኞች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚነዙት ጥላቻ ተአማኒነትና ድጋፍ
እንዲያገኝ ያስቻለው አብዛኛው የትግራይ ምሁር በተለይ በዲያስፖራ ዝምታን መርጦ
የማዶ ተመልካች መሆን መምርጡና የኢህአዴግ አገዛዝ የተጋሩ ብቻ እንደሆነ
በሚያስመስል ደረጃ የገዢው የህወሓት ቡድን ደጋፊዎችና ከግል ጥቅማቸው ውጭ
በአገርቤት ያለው የትግራይ ህዝብ ችግር ደንታ የማይሰጣቸው ሆድ-አደር ተጋሩ
በየኤምባሲው አገዛዙን ደግፈው የሚያደርጉት ሰልፍና አገልግሎት ነው።
ስለሆነም በተለይ በዲያስፖራ ያላችሁ ምሁራን የትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ ጠላቱ
ከሆነው ከህወሓት ቡድንና በጥላቻ ከታወሩ ጽንፈኞች ለመታደግና አሁን ኢትዮጵያ
ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት በሚደረገው ትግል በፈለጋችሁት መንገድ እንድትሳተፉና
መጫወት የሚገባችሁ ምሁራዊ ሚናችሁን እንድትጫወቱ ጥሪያችንን እናቀርብላችሁ
አለን። እንዲሁም ህወሓት/ኢህአዴግን ተደራጅታችሁ እየታገላችሁ ያላችሁ የትግራይ
ወጣቶች ትግላችሁን እንድታጠናክሩ፣ ያልተደራጃችሁም በፈለጋችሁትና ባመናችሁበት
መንገድ እንድትደራጁ፣ የተናጠል ትግል የትም ስለማያደረስ ደግሞ ትግላችሁን
በኢትዮጵያ አንድነትና በእኩልነት አብሮ መኖርን ከሚቀበሉ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን
ወጣቶች ትግል ጋራ እንድታስተባብሩ ጥሪያችንን እናቀርብላችሁ አለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ትግል ከገባችበት ቀውስ ትገላገላለች!!!
የኢትዮጵያዊያን ተጋሩ የውይይት መድረክ።
ከውይይት መድረኩ ለሚደረገ ግኑኝነት፣ EthiopianTegaruDF@gmail.com መጠቀም
ይቻላል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu