Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Breaking News Amharic, Ethiopian

የህወሃት የበቀል ሰይፍ በወልዲያ

Published Posted on by | By TZTA News
Spread the love

[በወንድወሰን ተክሉ-ጋዜጠኛ]
**መነሻ ጭብጥ-
** ማክሰኞ እለት በወጣው የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ ተቋሙ በወልዲያ
ከተማ የተካሄደውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዟል። ድርጊቱን የፈጸሙትና አዘው
ያስፈጸሙትም በአስቸካይ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው በሚል አቋም ጉዳዩ በነጻና ገለልተኛ
አጣሪ ሃይል እንዲጣራ ሲል ጠይቋል።
** ከተማይቱ ለ4ኛ ቀን በዓመጽ የዋለች ሲሆን በእለቱ መቆም የነበረበት ሳምንታዊው
የማክሰኞ ገበያ በወጣቶቹ በኩል የሞቱብንን ሀዘን ሳንጨርስና እያለቅስን ባለንበት ሁኔታ
ገበያው መቆም የለበትም በሚል በትነውታል።
** ማክሰኞ እለት የ13ንጹሃን ሰዎች በግፍ መገደላቸው የተረጋገጠ ቢሆንም የማቾቹ
ቁጥር ግን በተጠቀሰው አሃዝ ጋር በእጥፍና በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ በስፍራው ያሉ
ነዋሪዎች አንደበት መረዳት ተችሏል።[ከ20 በላይ እንደሞቱና በርካቶች ወደ መቶ
የሚጠጉ እንደቆሰሉ ይነገራል]
** ለምንድነው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ልብ ውስጥ በታላቅ አክብሮት
በሚከበረው ዓመታዊው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ አይደለም ከአስርና ከሃያ በላይ
ምእመን መግደል ይቅርና ለምንስ እና እንዴትስ ተብሎ ነው በሃይማኖታዊ በዓል ስፍራ
ገዳይ ጥይት ይዞ መገኘት ያስፈለገው?
** ለምንድነው በቅዱስ ጽላቱ ፊት የጽላቱ ዓማኝና አክባሪ በሆነው ላይ ጥይት መተኮስ
ይቅርና መሳሪያ የታጠቀ የሀገር ድንበር ጠባቂ የሆነው መከላከያ ሰራዊት እንዲሰማራ
የተፈለገው?
** ለመሆኑ ታቦተ ጽላቱ ክላሽና የጭስ ቦምብ በታጠቀ ሰራዊት መጠበቅ አለበትን? ጽላተ
ታቦቱ ጠባቂ ወታደር ያስፈልገዋልን? ጠባቂው ነው ተጠባቂ ወይንስ ተጠባቂው ነው
ጠባቂ?
ማነው ማንን የሚጠብቀው?
** ከመነሻው ጀምሮ ጽላተ ታቦቱን በክላሽንኮብ እና በአስለቃሽ ቦምብ ለማጀብ ሲወሰን
ለበዓለ ጥምቀቱ ድምቀትና ሞገስ ለመስጠት ታስቦ ሳይሆን በውስጥ የተጸነሰ እርኩስ
ሰይጣናዊ ዓላማና ሴራን የጸነሰን ሀሳብ የያዘ ትእዛዝ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።
ጽላተ ታቦቱ ከቀማኛና ዘራፊ ጠብቁኝ ያለ ይመስል ከመከላከያ፣ከፈጥኖ ደራሽና ከአድማ
በታኝ ክፍል የተውጣጣ ታጣቂ ሰራዊት ወደ ባህረ ጥምቀቱ ማሰማራት ታቦታቱን
በማክበር ለማንገስ የሚመጣውን ህዝበ ምዕመን አደጋ ያደርሳሉ በሚል ስጋትና ፍርሃት
ሳይሆን የተለየ ዓላማና ትእዛዝን ተቀብሎ እንዲገኝ የተደረገ ታጣቂ መሆኑን መናገር
የሚያስችለው የደረሰው አሰቃቂ ክስተት ነው።
** በወልዲያ የተጠቃው ማነው? አጠቃላይ ጥቃቱስ ለምንና እንዴትስ ተፈጸመ? እና
መሰል የሆኑ በርካታ መልስ ፈላጊ ጥያቄዎችን የሚያስጨረው የወልዲያው አሰቃቂ
ጭፍጨፋ የእያንዳንዳችንን ሁለንተናዊ እይታና ፍርድ የሚጠይቅ ጥቃት እንደሆነ ልናውቅ
ይገባል።
**1ኛ-በወልዲያ የተጠቃው ክፍል ማነው?
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አቻ ያልተገኘለት ሃያል ሃይልና ተቃም ቢኖር የእምነት ሃይልና
ተቃማት ናቸው። ብዙዎች ወደዚህች ምድር የመጡበት ዋና ምክንያት ከምድራዊው
ህይወት በሃላ ላለውና ዘላለማዊ ለሆነው ሰማያዊው ቤት መግቢያ የሚሆንን ተግባር
በሚያምኑት ዘርፈ ብዙ እምነት ስር ሆነው ለመማርና ለመፈጸም ነው ብለው ያምናሉ።
ለብዙዎች የህይወት በምድር መገኘት ዋና ዓላማ የቁስ አካል ክፍል የሆነውን ሀብት
ለማካበት ሳይሆን አምላካቸውን ለማገል እንደሆነ ያምናሉ። እናም እምነት በእያንዳንዱ
የሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራና ቦታ ያለው ገዢ ተቋም ሲሆን
በኢትዮጵያዊያን ዘንድም እጅግ በጠነከረ ሁኔታ ታላቅ ስፍራ፣ከበሬታ እና የገዢነት ሚና
ያለው እንደሆነ ይታመናል።
በወልዲያ ጥቃት የመጀመሪያው ሰለባ ይህ ታላቅ ሃይልና ተቋም የሆነው የእምነት ስፍራና
ስነስርዓት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው የእምነቱ ተከታይ፣አክባሪና አማኝ የሆነው
ህዝበ ክርስቲያኑ ሆኖ እናገኘዋለን።
የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈበትና የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያለበት ጽላተ ታቦት
በስርዓቱ ታጣቂዎች ክፉኛ ተንቆ ሲጠቃ መስማትና ማየት በማይፈቅደው ስብእናችን
ልናይም ሆነ ልንሰማ በቅተናል።
በእለተ ቅዳሜ ጥር 12ቀን የሚነግሰውን አመታዊ የቅዱስ ሚካኤልን ንግስ አጅበው ሲጋዙ
የነበሩ ወጣቶች ብቻ አልነበሩም በጥይት እሩምታ የተቆሉት። በአንጻሩም የሙሴን ጽላት
በክብር ተሸክመው ወደ መንበረ ማደሪያው ለመመለስ እያዘገሙ የነበሩ ቀሳውስቶችም
በአስለቃሽ ጭስ ቦምብ ተደብድበው ሲወድቁ ታይተዋል።
ጽላተ ታቦቱን የተሸከሙት ቀሳውስት በአስለቃሽ ጋዝ ጭስ እንዲደበደቡ የተደረገው
በእርግጥ ስርዓቱን የሚወርፍ ቃላትን ተናግረው ነው? ወይንስ ታቦቱ እራሱ ተቃዋሚ ሆኖ
ስርዓቱን ማወገዝ ስለጀመረ ነው ብለን ብንጠይቅም መልስ ሳናገኝለት ጽላቱን የተሸከሙት
ቄስ በተተኮሰባቸው አስለቃሽ ጋዝ ጭስ ተመተው ሲወድቁና በክብር የተሸከሙት የቅዱስ
ሚካኤል ጽላት ሲወድቅ ነው መስማት የቻልነው።
ከሁለትሺህ ዓመት በላይ እድሜ ያላት የኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን በታሪካ ካጋጠማት
ጨላማ ግዜዎች የዮዲት ጉዲት ዘመን እና የመሀመድ ግራኝና የደርቡሽ ወረራ ጥቃቶች
ወቅት እንደደረሰባት ክብራን የገፈፈ፣ማእረጋን የነጠቀና ቅድስናዋን ያጎደፈ ተግባር
በዘመናችን በራሳ ክርስቲያን ነን ባይ ገዢ ሃይል ሲፈጸምባት ለማየት ተገደድን።
አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ የሙስሊሙ መስጊድ ተቋማት በያሉበት ሁሉ ወንጀለኛና
ጥፋተኛ ከቅጣት እየሸሸ የሚሸሸግባቸው ስፍራዎች መሆናቸው አክትሞ ንጹሃን አማኞች
እራሳቸው በጥይት የሚቆሉበት ስፍራና ተቋማት መሆን ደረጃ የደረሱት በዚሁ በህወሃት
መራሹ ዘመን ነው።
በ1993ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የትምህርት ነጻነታችን ይከበርልን ጥያቄን
ባቀረቡበት ወቅት በዶ/ር ገነት ዘውዴ ፈቃጅነት ጥይትና ቆመጥ የታጠቀ ፖሊስ ወደ
ስድስት ኪሎው ዩንቨርሲቲ እንዲገባ በተወሰነበት ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች
እራሳቸውን ከአፈሳውና ከዱላው ለማዳን ወደ ቅድስት ማሪያም ቤ/ያን ሮጠው ተሸሽገው
ነበር።
የመንበረ ፓትሪያሪኩ ደብር የሆነችው ቅድስት ማሪያም ቤ/ያን እየሮጡ በመምጣት
የተሸሸጉባትን ተማሪዎች አላስጠጋም በሚል በራን ሳትዘጋባቸው የተቀበለች ቢሆንም
የወቅቱ ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ ፖሊስ ቤተክርስቲያኒቷ ቅጥር ግቢ ድረስ
ዘልቆ የተሸሸጉትን ተማሪዎች እየቀጠቀጠ እንዲወስድ ሲያደርጉ በስፍራው ተገኝተን
አይተናል።
ዛሬ ደግሞ በወሎዋ ወልዲያ ከተማ በዓመታዊው የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ወጣቶች ጸረ
መንግስት የሆነውን የሻምበል በላይነህን ዘፈን ዘፍነዋል በሚል ሰበብ ብቻ በቅዱስ ጽላቱ
ፊት በጭካኔ በጥይት ተደብድበዋል። ጽላተ ታቦቱም ሳይቀር በአስለቃሽ ጭስ ጋዝ
ተደብድቦ እስከመውደቅ ደርሳል።
ባለፈው ዓመት በለገጣፎ በአንዲት ሙስሊም ከንቲባ የቅዱስ ዩሃንስ ቤተክርስቲያን
የጨረቃ ቤት ነው በማለት እንዲፈርስ ተደርጎ ንዋየ ቅዱሳቱንም በኮንቴይነር አጉራ
በፖሊስ ጣቢያ እንደ እግዝቢት ለዓንድ ዓመት ያህል እንዲታሰር ሲደረግ ከአቶ ለማ
መገርሳ በስተቀር ቅዱሱን ጽላት እንዴት ይታሰራል ብሎ የሞገተም ይሁን የተናገረ
ፓትሪያርክም ሆነ ባለስልጣን አልነበረም።
ዘንድሮ አቶ ለማ መገርሳ እስረኛውን የቅዱስ ዮሃንስን ጽላት ከለገጣፎ ፖሊስ ጣቢያ
እንዲፈታ ከማድረግም በላይ 10ሺህ ካሬ ሜትር መሬትን ለቤ/ያኑ መገንበያ በነጻ
በመስጠት ባይገላግሉት መንግስት ነኝ የሚለን ስርዓት ከመጤፍም የቆጠረው አይደለም።
ህወሃት መራሹ ስርዓት ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ክፉኛ ንቋል፣ ታላቁን እና ሃያሉን
እግዚአብሔርንም ክፉኛ ንቆ ተጠይፋልም። ባለቤቱን ባይንቁ አጥሩን አይነቀንቁ
እንደተባለው ለቤተክርስቲያኒቱና ለአጠቃላይ እምነት ተቋማት ከበሬታ ቢኖረው ኖሮ
በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው ተቋማቶች ውስጥ ጠልቆ በመግባት መንፈሳዊ ተቋማቱን
በመንፈሳዊ አባቶች ሳይሆን በፖለቲካ ካድሬዎችና የዘር ተመራጮች ባያጥለቀልቀውና
ባላረከሰውም ነበር።
በወልዲያ ጥምቀት በዓልን ለማክበር በወጣው ህዝበ ምእመን ላይ ጥይት ተርከፍክፎ
ከሁለት አስር በላይ ንጹሃን ወጣትና ታዳጊ ህጻናት ሲገደሉ የመንበረ ፓትሪያርኩ
ጽ/ቤትም ሆነ ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ ለተገደሉት ሰዎች ህይወት አዝነው ሳይሆን
ለሚተዳደሩበትና በሀብትና በስልጣን ለከበሩበት ቤ/ያን ክብር ተቆርቁረው እንኳን
ያሰሙትም ቃል አልነበረም።
የቅዱስ ጽላቱን ተሸካሚ ቄስ ተጎድተው መውደቅና የጽላቱም አብሮአቸው መውደቅ
የአቡነ ማቲያስን ልብ ሊነካም ሆነ ሊያስቆጭ አልቻለምና ቢያንስ ቢያንስ “ልጆቹን እንካን
ገደላችሁ ግን ታቦቱን ለምን አጠቃችሁ ” የሚል ቃል እንካን ሊያናግር አልቻለም።
ቤተክርስቲያናችን በማን እየተመራች ያለችው? ህወሃት ለስልጣኑ ንጹሃንን በመግደል
ጀብድ ሲጠመድ ቤተክርስቲያኒቷ ለምንድነው ለስልጣና ትንሽ እንካን መስራትም ሆነ
መቆርቆርን ማሳየት የተሳናት?
በእርግጥ የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ ትምህርት የቀሰሙ አባቶች ናቸውን
ቤተክርስቲያኒታን እየመሩ ያሉት ወይንስ ሌጣ የሆኑ ካድሬዎች አባና ብጹእ እየተባሉ
ነው እየመራት ያሉት?
በወልዲያ በግፍ ከተገደሉት ከ20በላይ ወጣቶችና ታዳጊ ህጻናት ይልቅ ከሁለት ሺህ በላይ
እድሜ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተጠቃችው፣የተዋረደችውና
የረከሰችው ጎልቶ የበለጠ ይመስለኛል። በግፍ የተሰውቱን ወገኖቼን ህይወት በማሳነስ
ሳይሆን ከቤተክርስቲያኒቷ አጠቃላይ ስነታሪክና ካለባት ከባድ ሃላፊነት አንጻር ጥቃቱ
ይበልጥ ያጋለጠውና የፈረካከሰው የህወሃትን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የጠመጠመውን
ጭምብል በመሆኑ አንጻር ነው ይበልጥ የተጠቃችው ቤተክርስቲያኒታ ነች ልል
የቻልኩት።
** 2ኛ-ከወልዲያው ጭፍጨፋ ህወሃት የሚገኘው በረከት ወይስ መርገምት?
ብታምኑም ባታምኑም በወልዲያ ጭፍጨፋውን የፈጸሙትና ያስፈጸሙት የህወሃት
ባለስልጣናትና ታጣቂዎች ለህወሃታዊ በረከት ብለው [ሰው እየገደሉና እየጨፈጨፉ የምን
በረከት ልትሉ ትችላላችሁ] ቢሆንም ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ መርገምትን
እንዳሳቀፋቸው ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ማክሰኞ እለት ከወልዲያ ከተማ እንዲወጣ የተደረገው ገዳዩ ታጣቂ ሃይል ወደ
ከተማይቱም የገባው ከበዓሉ በፊት ሶስት ሳምንት ቀደም ብሎ እንደሆነ ታውቃል።
ጽላተ ታቦታቱ ከመንበራቸው ተነስተው ወደ ማደሪያቸው ጥምቀተ ባህር የሚሄዱበት
እለተ ሀሙስ ምሽት ጀምሮ ታጣቂዎቹ ህዝበ ምእመኑን ክፉኛ ሲተናኮሉና ሆን ብለውም
ነገር በመፈለግ ሁኔታ በዱላ ሲደባደቡ እንደነበረም ታውቃል።
በዚህም አልረካ ያሉት ወገኖች ቅዳሜ እለት የማቹን አቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በትልቁ
አዘጋጅተው መንፈሳዊ እንጂ ፖለቲካዊ ባለሆነው ክብረ በዓል ላይ መገኘታቸውን ስንረዳ
ምን ያህል ለጸብና ለግጭት እንደተዘጋጁ እንረዳለን።
ግጭቱ ሆን ተብሎ እንዲፈጠር መፈለጉና መታቀዱን የሚገልጹ በርካታ ነጥቦችንም
መጥቀስ ቢቻልም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቪ.ኦ.ኤው ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተ የተናገሩትንም
ማካተት ይቻላል።
እንደነዋሪዎቹ አገላለጽ ጥቃቱ ሆን ተብሎ የታቀደና የተዘጋጁበት የበቀል ጥቃት ነው
ሲሉ ይገልጹታል።
ከወራት በፊት በመቀሌው እስፖርት ክለብና በወልዲያው እስፖርት ክለብ መካከል
በተሚካሄደው ውድድር ምክንያት ግጭት ተነስቶ እንደነበረና የንበረት መውደም
እንደተከሰተ የምንዘነጋው አይደለም።
ይህ ግጭትም የቅዳሜውን የህወሃት ብቀላን በመውለድ ከሃያ በላይ ንጹሃንን አስገድሏል
ባይ ናቸው ነዋሪዎቹ።
የጥይት ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ሁኔታ እድሜና የተመቱበትን ሁኔታ ስንሰማ ቁልጭ ብሎ
የሚታየን ምስል የሰሜን ወሎ ፖሊስ ኮማንደር ነኝ ያሉን አቶ አማረ ጎሹ “ወታደሩ
ከአቅሙ በላይ በሆነ ሁኔታ ተገዶ” ተኩስ እንደከፈተ ሳይሆን ሆን ብሎ በየህንጻው ላይ
በተቀመጠ አልሞ ተካሽ እየተመረጠ የግድያ እርምጃ መወሰዱን ነው መረዳት
የምንችለው።
በቀል ለህወሃት እንደማር ጣፋጭ ነውና አይበቀልም ብሎ የሚሞግት ሃይል
ያለአይመስለኝም ያው ከህወሃቱ በስተቀር። ከወልዲያ በባሰ መልኩ በአዲስ አበባው ጃን
ሜዳ፣በጎንደርና በባህር ዳርም ህዝባዊ የሆነ ስርዓቱን የሚተች መፈክርና ዘፈን ሲዘፈንም
ሆነ ሲስተጋባ እንደነበረ ይታወቃል። የሰው ህይወት ያልጠፋበትም ግጭት መፈጠሩም
ይታወቃል። ሆኖም የወልዲያው ጽላቱ በህዝብ የሚጠበቅና የሚወደድ ቅዱስ ታቦት
መሆኖ ቀርቶ የህወሃት ቱባ ቱባ ባለስልጣናት የሆኑ ይመስል ህይወታቸውን ለማዳን
እርምጃ ወሰድን በሚል አገላለጽ የጥይት እርሙታ ሲያዘንቡ የታዩበት ዋና ምክንያት
በበቀል ሚሽን ላይ ስለሆኑ ነው ብለን የነዋሪዎቹን ገለጻ እንድናምን ያደረግናል።
በእርግጥ በወልዲያ ከሃያ የሚበልጡ ወድ ወገኖቻችን በግፍ ተገድለውብናል፣
የቤተክርስቲያኒታንም አባቶችን ከንቱ አባትነትና የለየለትን ካድሬነትን አይተንበታል –
የህወሃት ሰዎች ብቀላቸውን እንዳሳኩበት ቢገልጹም- እኛም ወገኖቻችንን በማጣት
ብንጎዳበትም ትልቁን መርገምትን የወሰዱት ግን ገዳዮች ህወሃቶች እንደሆኑ የማይሻር
እወነት ነው።
የወልዲያው ግድያ ከወሎና ሸዋም አልፎ ኦሮሚያ በመዝለቅ ለግዜው የሶስት ተማሪዎችን
ህይወት ቀጥፋል-ግድያውና መስዋእትነቱ ደግሞ ስርዓቱ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር
ሁሉን አደርጋለሁ፣ እስረኛን በሞላ እለቃለሁ” እያለ የፕሮፖጋንዳ ውሽክትናን
በሚወሻክትበት ወቅት የመሆኑ እውነታ ክስተቱ የስርዓቱን ህልውና እና የማይቀየር፣
የማይለወጥ ማንነቱን በማሳየት በኩል የሚጫወተው ሚና እጅግ ወሳኝና ጠንካራ መሆኑን
ሊሰመርበት ይገባል።
በህወሃቶች እጅግ የተናቀው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ከተናቀው ታላቁና ሃያሉ
የእግዚአብሔር ሃይል ጋር ሆኖ በህወሃት ልቦና እና አእምሮ ውስጥ ለሰከንድም ብልጭ
ብሎ የማያውቅን ታላቅ ክስተትን የሚያመጣበት ወቅት ቢኖር አሁን መሆኑን መግለጽ
ይቻለኛል።
በመላ ሀገሪቱ የተነሳው ህዝባዊ ዓመጽ የስርዓቱን የጀርባ አጥንት ኢኮኖሚ ክፉኛ
አንኮታኩቷል። የስርዓቱ ሃይል የሆነውን ኢህአዴግን ድርጅታዊ አንድነት ሰንጥቆ
አናግቷል። ህወሃትን በአንጃ ከፋፍሎ አዳክሟል። የተጋፈጠውን ህልውናውን አውዳሚ
ህዝባዊ ዓመጽን ለመመከት እስረኞችን የመፍታት አስገዳጅነትን የተቀበለውና
ተለውጫለሁ ባዩ ስርዓት ከቶም ቢሆን ለመለወጥ የማይችል ስለመሆኑ የወልዲያ ንጹሃን
ደም በመላው አማራ፣ኦሮሚያና ኢትዮጵያ በማይናወጽ እውነታ አሳውቋል።
እስቲ በጥቂቱ የጭፍጨፋውን ታቅዶና ሆን ተብሎ ተፈጻሚነትን የሚያሳዩ ተግባራትን
በነጥብ እናስቅምጥ-
1ኛ- ከሀሙሱ የከተራ በዓል ጀምሮ ህዝበ ምእመኑን በከፍተኛ የትንኮሳ እርምጃ በዱላ
ሲደባደቡ የነበሩና ቅዳሜና እሁድ እለት ጥይት ሲያርከፈክፉ የነበሩ ታጣቂዎች በሙሉ
ከበዓሉ ቀደም ብለው ወልዲያ እንዲገቡ መደረጉና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዳያውቁት
መደረጉ
2ኛ-በቅዱስ ሚካኤል በዓል እለት የማቹን መለስ ፎቶ በመያዝ ለእልቂቱ ምክንያት
የሆነውን ግጭት በማንሳታቸው
3ኛ-በየህንጻ ላይ የተመደቡ አልሞ ተኳሾችን ማዘጋጀት[ የሀገር መሪ ይገኛል እንዴ
በወልዲያ በምታክል አነስተኛ ከተማ ላይ ባለእስናይፐር አልሞ ተካሽ ታጣቂ
የተመደበው?]
4ኛ-በጥይት ቆስሎ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ የነበረን ታዳጊ ቁስለኛ ከመኪና አውርደው
“ጨርሰው”በማለት መረሸናቸው
5ኛ-ከተገደሉት ውስጥ በአምስት ጥይት ተደብድቦ የተገደለ መኖር
6ኛ-በጭፍጨፋው ወቅት የአከባቢው ፖሊስ ኮማነደርና የህወሃት አባል የሆነው አማረ ጎሽ
እጅግ ፈጥኖ ሰራዊቱ ተገዶ እራሱን ለመከላከል ሲል እርምጃውን የወሰደው ማለቱና
ጥፋተኛውን ተጨፍጫፊውን ህዝብ ማድረጉ
7ኛ-ከጭፍጨፋው በሃላ የፌዴራሉ መንግስትና ጽላተ ታቦቱም ጭምር የወደቀባት መንበረ
ፓትሪያርክ በጉዳዩ ላይ አንዳችም ቃል ሲሰነዝሩ አለመታየት
8ኛ-ጨፍጫፊዎቹ የተሰጣቸውን የጭፍጨፋ ግዳጅ ካጠናቀቁ በሃላ በማክሰኞ እለት ከተማዋን
ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውና
9ኛ-በታቦት ንግስ እለትና በሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ላይ ከከተማዋ ፖሊስ በላይ የታጠቀን
ሃይል በገፍ በማሰማራቱ
10ኛ-ጽላተ ታቦቱን በተሸከሙት ቀሳውስት ላይ አስለቃሽ ጭስ ቦምብ በመወርወር ታቦቱና
ቄሱ ሲወድቁ የቤሾፍቱን መሳይ ትርምስ ፈጥሮ ቁጥሩ የበዛ ምእመን በመግደል
በከተማይቱና በአጠቃላይም በመብት ጠያቂው ህዝብ ላይ የሞራል ስብራት ፈጥሮ
ለመበቀል እና የመሳሰሉት ወሳኝ ነጥቦች ጭፍጨፋው ሆን ተብሎ የታቀደ መሆኑን
አመላካች ድርጊቶች እንደሆኑ ማየት ይቻላል።
ጭፍጨፋው ስርዓቱ በሀገሪቷ ውስጥ ሀገራዊ መግባባትን እፈጥራለሁ በሚል ቃለ መሃላ
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የታሰሩ ፖለቲከኞችን በጣት የሚቆጠሩትን መፍታት
መጀመሩን ባበሰረበት ማግስት መሆኑ ስርዓቱ ከቶም ቢሆን የማይለወጥና በተለይም
ከቂመኝነቱና በቀልተኝነቱ የማይላቀቅ የመሆኑን እውነታ በይፋ የገለጸበት ክስተት
አድርጎታል።
መንግስትና ሃይማኖት ለየብቻ ናቸው የሚለውን ፕሮፖጋንዳንም አፈር ከድሜ በማስጋጥ
ቤተክህነትና ስርዓቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታነቱን በይፋ ያሳየበትና ብሎም የባእድ
ሰይጣናዊ አምልኮ ተከታይነቱን ቤተክርስቲያኒቷን እና ንዋየ ቅዱሳናን አራክሶ
በማጥቃቱ ይፋ ያደረገበት ክስተት እንደሆነም እንረዳለን።
ወልዲያ በእርግጥም የበቀልተኛው ህወሃት የበቀል ሰይፍ ያረፋበት ከተማ ነች።
የእግዚአብሔር ቃል በጎቼን በሃይል፣በጭቆና እና በግፍ ገዝታችሃቸዋልና በጎቼን
እንዳታሰማሩ ተቀብያችሃለሁ ይላል። የህወሃት በኢትዮጵያ ምድር ገዢነት ያበቃለት
ቢሆንም ፍጻሜ ግን ገና የሚቀረው የተተፋና የተጠላ ገዢ ሆናል።
ቸር እንሰንብት!!
**ማስታወሻ-ለውድ አንባቢያን –
ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮ ሚዲያ ድረ ገጽ ላይ ዘወትር ሰኞ እና ዓርብ ወቅታዊ የህገራችንን
ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ከአፍሪካ ቀንድና የዓለም ሁኔታ ጋር
እያቀናጀሁ የማቀርብላችሁ መሆኔን እየገለጽኩ ትከታተሉ ዘንድ በአክብሮት ሳሳስብ
የተለመደው ድጋፋችሁና አስተያየታችሁ እንደማይለየኝ ተስፋ በማድረግ ነው።
—————-
አስተያየታችሁን ወይም ጥያቄም ካላችሁ በኢትዮሚዲያ ኢ-ሜይል
ወይም teklu7@gmail.com ብላችሁ በግሌ ብትጽፉልኝ በአክብሮት እመልሳለሁ


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu