Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Ethiopian

የአለም ባንክ እውነትና ኩሸት! – ኤርሚያስ ለገሰ

Published Posted on by | By TZTA News

የአለም ባንክ እውነትና ኩሸት! – ኤርሚያስ ለገሰ

Spread the love
By ሳተናውSeptember 29, 2017 14:30
      

ኤርሚያስ ለገሰ

ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የአለም ባንክ ሪፓርት ብዙ የሚነግረን ቁምነገሮች አሉ። በአንድ በኩል የሕውሐት አገዛዝ የገባበትን ማጥ ያሳየናል ። ይህም አገዛዙ ጊዜውን ጠብቆ ተፈጥሮአዊ ሞቱን ሊሞት መቃረቡን ሐገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚያሳዩበት ነው። በሌላ በኩል አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ምእራባውያን በሚያካሂዱት ስውር ደባ ስርአቱን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን አገም ጠቀም እንመለከታለን ። እነዚህ የውጭ ሐይሎች እውነትና ውሸት እየመጋገቡ የሚያቀርቡት በዚህ ምክንያት ነው። የሰሞኑ የአለም ባንክ ሪፖርት ለዚህ አባባል ጥሩ ምሳሌ አድርጌ ወስጀዋለሁ። ለዚህ ብዙ ማስረጃዎች ከሪፖርቱ ውስጥ መጥቀስ ይቻላል። ለዛሬው አንድ ኩሸት እና እውነት እንውሰድ።

 

                             ኩሸት አንድ: ” ዳታ ማጣጣም!”

በሕውኃት/ ኢሕአዴግ ውስጥ ” ዳታ ማጣጣም” የሚባል ልምድ አለ። ይህ ልምድ የተወሰደው ከአለም ባንክ ነው። የአለም ባንክ እስከ ጐጥ የዘለቀ መዋቅር ስለሌለው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያቀርብለትን የእድገት አሃዝ ይቀበላል። በሂደት ይሄ ባለሁለት አሃዝ ( በአብዛኛው 11%) የተጋነነ መሆን እና እዛው ቁጥር ላይ ሙጭጭ ማለት እንዲሁም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የተነጠፈው እውነት መረጃው ውሸት መሆኑን ይገነዘባል። በዚህ ምክንያት አለም ባንክ እስከ አስር የሚጠጉ ሠራተኞቹን ወደ መዲናችን አዲስአባ በመላክ በቁጥሮቹ ላይ ይደራደራል። አብዛኛውን ጊዜ አለም ባንክ ከ5 እስከ 8 % እድገት ይገልጣል። በነገራችን ላይ የባንኩ ሰዎች ተጨማሪ ፈንድ ለማግኘትና ለግላቸው ጥቅም ሲሉ እድገት መጥቷል ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። አለበለዚያ የእንጀራ ገመዳቸውም ሊዘጋ ይችላል። አለበለዚያ ፈንዱን በማስገኘታቸው ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅምም አይኖርም።  ህውሓት በበኩሉ የ11% እድገት ይዞ ይቀርባል። ከዛም ድርድሩ ይጀምራል።

በመጨረሻም በድርድር የፀደቁት( በአብዛኛው አማካይ) ቁጥሮች የአለም ባንክ ዳታ ሆነው ይቀርባሉ። በዚህ አሃዝ መሰረት ባንኩ ፈንዱን ያገኛል፣ ህውሓትም የፕሮፐጋንዳ ማድመቂያውን ያገኛል። አቶ በረከት “አለም የሰጠነውን ስለሚቀበል ጨማምራችሁ ከመስጠት አትቆጠቡ!” የሚለው ይሄንን ስለሚያውቅ ነው። በረከት ይሄን አይልም የምትሉ ሰዎች “የሁለት ምርጫዎች ወግ ገጽ 30 ተመልከቱት።

ከፊሉ እንዲህ ይላል፣

“—- የግንቦት ሃያን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሚዲያው ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና እንደገሰገሰች ለሶስተኛ ጊዜ ባለሁለት አሃዝ ማስገንዘባችን ሁሉም ነገር መጥፎ እንዳልሆነ አበሰረ። ሚዲያው ፊቱን ወደ ልማት አጀንዳ አዙሮ ጉዳዩ የህዝብ መነጋገሪያ መሆን ሲጀምር አለም አቀፍ ሚዲያው እግር በእግር ተቀብሎ አስተጋባው። አለም የአገሬው ህዝብና መንግስት የሰጡትን ሊቀበል እንደሚችል ታየ። ስለራሳችን መጥፎ በነገርነው ቁጥር ይህንኑ እንደ ገደል ማሚቴ ሊያስተጋባ፤ ጥሩ ስንነግረውም ያንኑ ሊቀበል እንደሚችል አረጋገጥን።”

 

የአለም ባንክን ዳታ ማጣጣም ውሸት በአንድ ምሳሌ አስደግፈን እንመልከተው ። ሪፖርቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሶስተኛው (33 ሚሊዬን) የሚጠጋው ከፍፅም ድህነት ወለል በታች በቀን ከ1•9 ዶላር በታች ገቢ ያገኛሉ ይላል። ከሁለት ዶላር በታች የሚለውን ስሌት ከሄድን “የጠቅላይ ሚኒስትሩን” (HD) ቤተሰብ ጨምሮ በድህነት ወለል ውስጥ እንከታቸዋል። ነብስ ይማርና “ከድርጅት ተቆራርጦ የሚቀረን አራት ሺህ ብር ነው!” የተባለላቸው የአቶ መለስ ቤተሰቦች ደግሞ በፍፅም ድህነት ውስጥ ኖረው የሞቱ ይሆናሉ። እንደውም ከዛሬ ጀምሮ ” ምጡቁ”፣ ” ዘመን ተሻጋሪ!”፣ ” የክፍለ ዘመን ክስተት!” እየተባለ መንፈሳቸው ከሚጨነቅ ” የደሃ ደሃ” ብንላቸው በሰማዩ ኑሮአቸው እረፍት የሚያገኙ ይመስለኛል። የህ ከሆነ ሴትየዋ ጉልት ለመነገድ ያቀረበችው ሓሳብ በሕወሓት ደጃፍ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል ። “ጉልት ሸጦ የመክበር ሓሳብ! በሓሳብ ላይ ሓሳብ! ዋናው ገንዘብ አይደለም ሓሳብ ነው!!” አዜብ መስፍን አንዳለችው!!

አሁን ደግሞ አንድ መሬት የወረደ ተጨባጭ ምሳሌ እናንሳ። ሁለት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራን የሆኑ ባልና ሚስት አሉ እንበል። በድጋሚ እነዚህ ባለትዳሮች አራት ተማሪ የሆኑ ልጆች አሏቸው እንበል። እነዚህ ጥንዶች የወር ደሞዛቸው በድምሩ 10ሺህ ብር ይሁን። እንግዲህ በአለም ባንክና አለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ካየነው ይሄ ቤተሰብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው። እስቲ እግዜር ያሳያችሁ እነዚህ የዪንቨርስቲ መምህራን ቤተሰቦች ከድህነት ጠለል በታች የሚኖሩ ከሆነ እንዴት 33 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ በፍጹም ድህነት ይኖራል? የተጨበጠ ቁጥር የለኝም እንጂ ከ100 ፣ሚሊዮን ህዝብ 90 ሚሊዮኑ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንደሚኖር አልጠራጠርም:: የተወዳጅ ፓርላማ አባላት ከድህነት ጠለል በታች ናቸው። የተከበሩ ሚኒስትሮቻችን በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። የክልል ፕሬዝዳንቶችና የካቢኔ አባላት ከድህነት ወለል በታች ናቸው። ከዩንቨርስቲ እስከ አንደኛ ደረጃ የሚያስተምሩ መምህራንና ቤተሰቦቻቸው ከድህነት ወለል በታች ናቸው። ታዲያ ማን ቀረ?

በመሆኑም ይህ የባንኩ አሳሳች መረጃ በዳታ ማጣጣም የተገኘውን መረጃ እንደ እውነት ከወሰድነው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገሮች ያላት ደረጃ አስገራሚ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ በመቶኛ ሲሰላ ከኢትዮጵያ ይበልጣል። በደቡብ አፍሪካ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ 55.5% ያህል እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ይሄ ማለት ከሁለት ደቡብ አፍሪካዊ አንዱ በቀን ከ 1.9 ዶላር በታች ገቢ ያገኛል። በሌላ በኩል ከሶስት ኢትዮጵያዊ አንዱ ብቻ በቀን ከ1.9  ርበታች ያገኛል። ይህ ውጤት የሚያመለክተን ነገር ቢኖር የተሻለ ገቢ ለማግኘት ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ሳይሆን፤ ደቡብ አፍሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ነበረባቸው።

ሐቁን እንነጋገር ከተባለ አለም ባንክ በዳታ ማጣጣም ያወጣው የድህነት መለኪያ በኢትዮጵያውያን ቁስል ላይ እንጨት ከመሰደድ የሚተናነስ አይደለም። ባንኩ በድህነት ምክንያት ባህርና የዱር አውሬ የበላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ አላግጧል።  በሳውዲ አረቢያ የአረብ ካራ የሚጠብቃቸው ግማሽ ሚሊዮን ሴት እህቶቻችን ላይ ቀልዷል። በደቡብ አፍሪካ የመኪና ጎማ አንገታቸው ላይ ተንጠልጥሎ የተቃጠሉትን ወጣቶች ስቃይ ከቁብ አልቆጠረውም። ድህነቱ በፈጠረበት ጫና ምክንያት አገሩን ለቆ እንደ ጨው የተዘራውን ኢትዮጵያዊ ጥፋተኛ ማድረግ ነው። የእለቱ ደራሽ ምግብ አጥቶ ወደ ሞት አፋፍ እየተሸጋገረ ያለውን 10 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ላይ ክህደት መፈጸም ነው። ከብቶቻቸው ሞተውና ራሳቸው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያሉትን ግማሽ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሱማሌዎች “አፍንጫችሁን ላሱ!” ከማለት የሚተናነስ አይደለም። የአለም ባንክ ሰዎች “እኔን ከደላኝ ሌላው አፈር ደቼ ይብላ!” የሚል አቋም እንዳላቸው የፈነጠቁበት ነው። ለጠንካራ አገላለጤ ይቅርታ ይደረግልኝና አለም ባንኮች ሀገር ሲፈራርስ ህዝብ ለመበታተንና ሲከፋም ለርስ በርስ እልቂት ሲመቻች ደንታቸው እንዳልሆነ አሳይተውናል። ያየነውና እያየነው ያለነው እውነት ይሄ ነው። ሁለት ትላልቅ ዝሆኖች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በዳታ ማጣጣም ሲራገጡና በእጅ መንሻነት ሲደራደሩ ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።

 

ለሁሉም ግልጥ እንደሆነው ድህነት ዘርፈ ብዙ ነው። በምግብ እጦት፣ በትምህርት እጦት፣ በውሃ እጦት፣ በጤና አገልግሎት እጦት፣ በመንገድ እጦት—– ወዘተ ይገለጻል። በየአገራት ያለውን የደህንነት መጠን ለመለካት በአሁን ሰአት በጥቅም ላይ ከዋሉ መለኪያዎች “ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ ኢንዴክስ’’ የሚባለው ይገኝበታል። ይህ ዜጎች በተጠቀሙበት ምርትና አገልግሎት መጠን የሚለካ ተቋም በየአመቱ የአገራትን ደረጃ ያወጣል። የዛሬ ሶስት አመት በኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ታትሞ በወጣው በዚህ የአለም አቀፍ ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ መመዘኛ ኢትዮጵያ አስከፊ ድህነት የተንሰራፋበት በአለም ሁለተኛዋ የመጨረሻ ደሃ አገር ናት። ወደ ኋላ የምናያት አገር አፍሪካዊቷ ኒጀር ብቻ ናት። በዚህ መለኪያ መሰረት 87.3% ኢትዮጵያዊ በአስከፊ ዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ የሚማቅቅ ነው። በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ከሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ 96 በመቶው በአስከፊ ዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ የሚማቅቅ ነው።

 

ባለፉት ሁለት አመታት በህዝቡ ውስጥ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ የተከሰተው ረሃብና ድርቅ፣ በጎሳ ግጭት ምክንያት የተፈናቀለው ህዝብ፣ መንግስት መራሽ የመሬት ንጥቂያና ዝርፊያ፣ የውጭ ንግድና ቱሪዝም ማሽቆልቆል፣ ከኢትዮጵያ እየተዘረፈ የሚወጣው ገንዝብ ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ መሆን፣ ነጋዴው ግብር አልከፍልም በማለት ያስነሳው ተቃውሞ፣ በመጨረሻም አገዛዙ ለአንድ አመት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአስከፊ ድህነቱን መጠን ከፍ ያደርገዋል እንጂ ሊቀንሰው አይችልም። በተጨባጭ እንደሚታየው በምግብ እህል እጥረት ምክንያት በየቀኑ የዋጋ ንረት እየታየ ነው። በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አለመኖር እንኳን ኢንዱስትሪ ሊገነባ ዩንቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች ዳቦ ተጋግሮ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ከአገዛዙ ሚዲያዎች እየሰማን ነው። ለአብነት ያህል ዛሬ መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ ም የወጣው የብአዴን ድርጅታዊ መግለጫ “የመብራት አገልግሎት በህዝባችን ዘንድ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ መሆኑን በጥልቀት ገምግመናል” ይላል። እሰየው የሚያስብል ግምገማ ነው። ብአዴን የሚቀረው ነገር ቢኖር አማራ ክልልን በጨለማ እንዲዋጥ ሲያደርግ ህዉሃት ትግራይን ደምቃ እንድትታይ ለምን አደረጋት የሚለውን መገምገም ይሆናል።

 

በነገራችን ላይ ይሄ አለም ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ” ዳታ የማጣጣም ” ተሞክሮ ዛሬ በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ፣ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ማእከላዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን መደበኛ አሰራር ሆኗል። የመጥፎ ልምድ ሌላኛው መገለጫ ! ቶጐ ጫሌ የሚገኘው የቀበሌ ሊቀመንበር እና አብርሃ አጽብሃ የሚገኘው የሕውሓት ካድሬዎች የሚያቀርቡት የኢኮኖሚ እድገት ቁጥር አንድ አይነት ነው። አንድ አይነት። 11 በመቶ። ዳታ በማጣጣም የተመዘገበ ባለ ሁለት አሃዝ እድገት።

 

                እውነት አንድ :- ” እኩል ተጠቃሚነት የለም!”

ሪፖርቱ “የኢኮኖሚ እድገቱ በክልሎች እና በሕዝቦች መካከል እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አላረጋገጠም” ይላል። እኛስ ከዚህ ውጭ ምን አልን? ምን ወጣን? አሁንም ለመድገም ያህል የሕውኃት አገዛዝ በዘር ላይ የተሞረከዘ በመሆኑ መቼም ቢሆን በእኩልነት ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እድል መፍጠር እንደማይችል በተደጋጋሚ ገልጸናል ።

እርግጥም በማበላለጥ ፣ በጥላቻና በጠላትነት የተመሰረተው የአገዛዝ ስርአት ውጤቱ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም ። ጎጠኝነትና ጠባብነት የተከለው የመርዝ ዛፍ ፍሬውም መርዛም መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ዘለግ አድርገን ካየነው ይህ አንዱን ክልል ከሌሎች ለይቶ የማበልፀግና ሌላውን የማቆርቆዝ አድሎአዊ አሰራር በትውልዶች መካከል ከቶውንም ሊረሳ የማይችል የቂም በቀል ቋጠሮ የሚያኖር ነው። አንዱ አካባቢ እንደ የቁማሯ የአሜሪካ ከተማ ላስቬጋስ በምሽት ፀሐይ ተንቆጥቁጦ ሌላው በድቅድቅ ጨለማ ሲዋጥ የሚያመላክተን ነገር የአገዛዙን አድሎአዊነት እና ሸውራራ አመለካከት ነው። የዘረኝነት ፓሊሲ የወለደው ጐሰኝነት ነው።

አንዳንዶች ጐሰኝነትን ቀባብተው ብሔርተኝነት ቢሉትም በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይ ለፓለቲካ መሳሪያ እስከተጠቀምንበት ድረስ ሁለቱም የዘረኝነት ፓሊሲ ነው። ለራስ ብሔረሰብ ሰው ድጋፍና ጥቅም የመስጠት አድሎአዊ አካሄድ ነው ። ለአጠቃላይ የአገር እድገት ሳይሆን በራስ ክልል ለሚካሄድ ልማት ቅድሚያ መስጠት ነው። አለም ባንክ አፋን ሞልቶ የአድሎው ምንጭ ጐሠኝነት የወለደው አይበል እንጂ መብራቱና መንገዱ በልዩ ትኩረት የት እየተሰራ እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ነግሮናል። የባንኩ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ማይክል ጊገር የአገሪቱ እድገት ሁሉም አካባቢዎችና ዜጎች ማካተት እንደሚገባው፣ የኢኮኖሚ ርቀቱ መጥበብ እንዳለበትና መሠረተ ልማቶች ያለ አድሎ መስፋፋት እንደሚገባው በትኩረት ተናግረዋል ። የፈረንጁ ምክር ” የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር” ቢሆንም ከምክሩ ባሻገር ያለውን እዉነታ አሻግሮ ለማየት ይረዳል። ማየታችንን ካልከለከሉን በስተቀር!!

Top of Form


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu