Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Breaking News Amharic, Ethiopian

የአደዋ ጦርነት፣ የሂዎት እና የውጫሌ ውሎች ታሪካዊ ግንኙነት፣ (በ ደረጃ ተፈራ የካቲት 22/ 2009 ዓ.ም )

Published Posted on by | By TZTA News

የአደዋ ጦርነት፣ የሂዎት እና የውጫሌ ውሎች ታሪካዊ ግንኙነት፣ (በ ደረጃ ተፈራ የካቲት 22/ 2009 ዓ.ም )

Spread the love
ለአደዋ ጦርነት መነሻነት እንደምክንያት የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 እንደ ሆነ ይገለጽ እንጂ ዋናው መንስኤው ግን ጣሊያን ምጽዋን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ  በቀኝ ግዛቱ ሥር ለማድረግ በነበረው እቅድ ነበር። መጀመሪያውኑ ጣሊያን ምጽዋን እንዴት ሊይዝ ቻለ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ፦ እንግሊዝ ናት ምጽዋን ለጣሊያን አሳልፋ የሰጠችው። እንዴት? ታሪኩ እንዲህ ነው፣ በዛ ጊዜ ደርቡሽ (ሱዳን) አመጽ አስነስተው በድንገት በሱዳን ውስጥ የሚገኙ እንግሊዞችን ከበቧቸው። ዮሐንስ ደርቡሽን (መሃዲስቶችን) በመውጋት እንግሊዞችን እንዲያስለቅቁ፣ እንግሊዝ ደግሞ በአጸፋው ምጽዋን ከቱርክ ለኢትዮጵያ እንድታስመልስ ተዋዋሉ። በውላቸው ላይ ከእንግሊዝ ፍቃድ ውጭ ኢትዮጵያ ምጽዋ ላይ ምንም ዓይነት ጦርነት ማድረግ እንደማትችል የሚገልጽ አሳሪ አንቀጽ የያዘ ውል ተካተተበት። ውሉን የእንግሊዝ ተወካይና አጼ ዮሐንስ ይፈራረማሉ። ይህ ስምምነት የሂዎት ውል / Hewett Treaty/ ተብሎ ይታወቃል።  
 
እናም እንግሊዝ ቱርክን ከምጽዋ ካስለቀቀች በኋላ አጼ ዮሐንስን ችላ ብላ ለጣሊያን አሳልፋ ሰጠች። ጣሊያንም ቀስ በቀስ እንደ ፍልፈል ወደ ውስጥ መስፋፋትን ጀመረ። ይህ ሁሉ ሲሆን አጼ ዮሐንስ ምን አደረጉ? ዮሐንስማ ምጽዋ ላይ የሰፈረውን ጠላት ጣሊያን ወግቶ እንደማባረር ለእንግሊዝ ጣሊያንን ከምጽዋ አስወጡልን የሚል ማመልከቻ አስገቡ። ለምን? ዮሐንስ ለእንግሊዝ በፈረሙት በሂዎት ውል ምክንያት።  
 
ስለዚህ አጼ ዮሐንስ የፈረሙት የሂዎት ውል ከመነሻው ችግር የነበረበት፣ የኢትዮጵያን ሉአዋላዊነት (sovereignty) አሳልፎ ለእንግሊዝ የሰጠ አስጠቂ ውል ነው። እዚህ ላይ ልብ በሉ! ምኒሊክ ግን በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ላይ ጣሊያን በራሱ ቋንቋ የሰፈረውን አስተርጉመው እኔ እንደዚህ አላልኩም እምቢ አልቀበለውም ሃገሬ ከማንም የበታች አይደለችም፣ ሞግዚትም አትሻም በማለት ለአውሮፓ ሃገራት ኢትዮጵያ ሉአዋላዊት ሃገርነቷን ለማሳወቅ በቅድሚያ ደብዳቤ በተኑ። ህጋዊነታቸውን ለዓለም መንግስታት ካሳወቁ በኋላ ወደ አድዋ ጦርነት ዘመቱ። የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረው ጣሊያንን አሸነፉ። 
 
ወደተነሳንበት ከምጽዋ የባህር ወደብ ተነስቶ ወደ ውስጥ የጣሊያንን የመስፉፉት ሁኔታ ስንመለከት በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አጼ ዮሐንስ እንግሊዝን እባክሽ ጣሊያንን ከምጽዋ አስወጪልኝ የሚል የንጉስ ሳይሆን የታዛዥ አሽከር አይነት የልመናና አስጥሉኝ ዓይነት ደብዳቤ ጻፉ። እንግሊዞች ምን ምላሽ ሰጧቸው? አፌዙባቸው። ከዛስ? ጣሊያን አስመራንና ከረንን አልፈው እስከመረብ ምላሽ ድረስ ተቆጣጠሩ። በሌላ አነጋገር ወደውም ሆነ ተገደው ዮሐንስ ኤርትራን እስከ መረብ ምላሽ ድረስ ለጣሊያን አሳልፈው ሰጡ። ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ እዳው ለምኒልክ ተረፋቸው።
 
አጼ ምኒሊክ የውጫሌን ውል ያደረጉት አጼ ዮሐንስ ኤርትራን እስከ መረብ ምላሽ ከሰጡ ከብዙ አመታት በኋላ የተደረገ ነው። አጼ ምኒልክ ወደ ኋላ ሄደው ዮሐንስ በህይወት ሳሉ ከእንግሊዝ ጋር የገቡትን የሂወት ውልና የፓለቲካ ስህተት መቀየር ባይችሉም የቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል ለመግዛት የመጣውን ጣሊያን አድዋ ላይ አሸንፈው መረብ ምላሽ ላይ በማቆም ቀሪውን የሃገራችንን ክፍል ከተስፋፊው ፋሽስት ጣሊያን ነጻ አድርገዋል፣ ታድገዋል። 
 
 
 
ወደ ኋላ ልመለስና አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ። አጼ ዮሐንስ ሃገር እንደሚመራ ንጉስ ምጽዋ ላይ የሰፈረውን ጠላት ጣሊያን ወግቶ እንደማባረር ለእንግሊዝ አስወጪልኝ የሚል የተማጽኖ ዳብዳቤ ጻፉ ለሚለው፣ የዮሐንስ ጭፍን ደጋፊዎች እውነቱን ለማምታታት ሰሃቲ እና ዶጋሊ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ከጣሊያን ጋር የተደረገን ጦርነት ሲያነሱ ይሰማል። እነዚህ ጦርነቶች በዮሐንስ ትእዛዝ የተፈጸሙ አይደሉም። የሰሃቲ እና የዶጋሊ ጦርነቶች ከዮሐንስ እውቅና እና ፍቃድ ውጪ በራስ አሉላ አባ ነጋ የተደረጉ ናቸው።
 
 
 
የጣሊያኖችን ማቆሚያ የሌለው መስፋፋት እና የንገሱን ቸልተኝነት መታገስ ያልቻሉት ራስ አሉላ አባ ነጋ አይኔ እያየ ሃገሬ ስትወረር አላይም በማለት ሰሃቲ እና ዶጋሊ በሚባሉ ቦታዎች በተለያየ ጊዜ ከጣሊያኖች ጋር ጦርነት በማድረግና ወራሪውን ለጊዜውም ቢሆን የጣሊያንን መስፋፋት የገቱት ቢሆንም ንጉሱ የሃገር ጉዳይነቱን በመተውና አሉላ ለስልጣኔ ያሰጋኛል በሚል መሠረተ ቢስ የሆነ የእንግሊዝ ወሬ ሰምተው ያለኔ ፍቃድ ለምን ከጣሊያን ጋር ጦርነት ገጠምክ ወደሚል ተራ የግል ጥል ውስጥ ገቡ። በዚህም የተነሳ ዮሐንስ መቀመጫቸውን አስመራ በማድረግ እስከ ምጽዋ ድረስ በመወርወር ጣሊያንን ሲያስጨንቁ የነበሩትን ጀግናውን ራስ አሉላን ከስልጣናቸው በማንሳታቸው የተነሳ የተፈጠረን ክፍተት በመጠቀም ጣሊያን አስመራንና ከረንን አልፈው እስከመረብ ምላሽ ድረስ ተቆጣጠሩ። ስለዚህ ምኒልክ ከአጼ ዮሐንስ የተረከቧት ሃገር  ኤርትራን የማያካትት ከመረብ ምላሽ የሆነች ሃገርን ነው ማለት ነው። 
 
 
 
በሂወት ውል አጼ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ጥቅምና ሙብት ለእንግሊዝ አሳልፈው ሰጡ፣ ከጎረቤት ደርቡሾች ጋር ጠላትነት በመፍጠር ለጎንደር መተማ መውደም (በደርቡሾች መቃጠልና መዘረፍ) እንዲሁም ለራሳቸው ለዮሐንስም ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ፣ ለመረብ ምላሽ ወይም ኤርትራ በጣሊያን መያዝ እና ኢትዮጵያን እርስ በርሱ ተያያዥነት ወዳለው እስካካሁንም ድረስ ወዳለቀቀን የኮሎኒያሊዝም ርዝራዥ ችግር ውስጥ የከተተን አስጠቂ የሆነው ውል ነው።
 
 
 
የሂወት ውል ባይኖር ጣሊያን ምጽዋ ላይ ባልሰፈረ፣ ጣሊያን ምጽዋ ላይ ካልሰፈረ ደግሞ የኤርትራ መረብ ምላሽ ችግር ባልኖረ፣ ስለዚህ የውጫሌ አንቀጽ 17 ውል አይታሰብም፣ ኤርትራም ከኢትዮጵያ አትለይም ወዘተ ወዘተ። እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንደ ሰንሰለት (Chain reaction) ተከታትለው የመጡት ችኩልነትና ጀብደኝነት የሚያጠቃቸው የፓለቲካ ብስለት የሌላቸው አጼ ዮሐንስ የሂወትን ውልን ዘለው ለእንግሊዝ በመፈራረማቸው ነው።
 
 
 
ከአፋር በረሃ ሽፍታነት ተነስተው የነገሱት ካሳ ምርጫ (አጼ ዮሐንስ) መጀመሪያ የባህር በራችንን ክፍት በማድረግ ለእንግሊዝ ወራሪ ጦር በማጋለጥ መንገድ እየመሩ አጼ ቴዎድሮስን እንደ ይሁዳ ለሞት አጋልጠው ሰጡ፣ ለዚህ ውለታቸው ከእንግሊዝ በተሸለሙት የጦር መሳሪያ በመታገዝ ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ የነገሱትን አጼ ተክለ ጊዮርጊስን በመማረክ ዓይናቸውን እንደ አረመኔ በጭካኔ በወስፌ ጎልጉለው በማውጣት አሰቃይተው በመግደል ንጉስ መሆን የቻሉት አጼ ዮሐንስ ከመጀመሪያው እጃቸው በደም የተጨማለቀ ጀብደኛ የጠመንጃ ሰው እንጂ ግራ ቀኙን የሚያስተውሉ በሳል አርቆ አሳቢ፣ የተረጋጉ የዲፕሎማሲ ሰው ስላልሆኑ የምጽዋ ነገርንና የጣሊያንን እያደር የመስፋፋት ጉዳይን የሚያስተካክሉበት መንገድ ጠፍቷቸው የጦር ጀነራላቸውን ራስ አሉላን አግለው ግራ በተጋቡበት ጊዜ መሃዲስቶች ጊዜ ጠብቀው ለበቀል ድንበር ተሻግረው መተማ ጎንደርን በመውረር አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን አቃጠሉ፣ ህዝቡንም ዘረፉ የሚል ወሬ በመስማታቸው ወደዛው ሲበሩ ሄዱ። ይሁን እንጂ መጥፎ እድል አጋጥሟቸው ሳይመለሱ ቀሩ።
 
 
 
ነገሩን ስናጠቃልለው ምኒልክ የውጫሌውን ውል አንቀጽ 17 መቃወማቸው ለኢትዮጵያን ሉአላዊነት (sovereignty) መቆማቸውንና በዚህም ምክንያት  ወደ አድዋ ጦርነት ማምራታቸውን ሲያሳይ በተቃራኒው ደግሞ ዮሐንስ ከእንግሊዝ ጋር የገቡት የሂዎት ውል ግን ሃገራችንን ያዋረደና ለአውሮፓ ቀኝ ገዢዎች መንገድ የከፈተ፣ ለምጽዋ መያዝ፣ ለኤርትራ መፈጠር መነሻ ምክንያት የሆነ ሃገራችንን ለጥቃት ያጋለጠ እስጠቂ ውል ነው።
 
 
 
ምኒልክ የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብረው ሺ ኪሎ ሜትር በመጓዝ አድዋ ድረስ ዘምተው አባቶቻችን የህይወትና የአካል መስዋእትነት ከፍለው ጣሊያንና ትግሬ ባንዳን ባያሸንፉ ኖሮ አጼ ዮሐንስና ልጆቻቸውማ ለሰላቶ ጣሊያን አሳልፈው ሰተውን ነበር።
 
ዘላላማዊ ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!
ክብር ለብልሁ መሪ ለአጼ ምኒልክ!
————-//————–
ደረጃ ተፈራ
የካቲት 22/ 2009 ዓ.ም (March 1, 2017)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu