Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Ethiopian

Published Posted on by | By TZTA News
Spread the love

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው ከሚጓዙት ሰዎች መካከል 2 ህጻናት ታፍነው ሞቱ
     
     መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም  ኢሳት ዜና:-በዛሬው እለት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልል በሀይል ተፈናቅለው ወደ ክልላቸው በመጓዝ ላይ ከነበሩት የአማራ ተወላጆች መካከል ሁለት ህጻናት ታፍነው መሞታቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪ  ለኢሳት ገልጸዋል።
     እያንዳንዳቸው ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ የአማራ ተወላጆችን የጫኑ 6 አይሱዙ መኪኖች ወደ አማራ ክልል የተጓዙ ሲሆን፣ ሁለቱ ህጻናት በመንገድ ላይ የሞቱት አየር አጥሯቸው ነው። እናታቸው ልጆቿን አልቅሳ በወጉ ሳትቀብር በረሀ ላይ እንዲጣሉ መደረጉን  ነዋሪው ገልጸዋል።                                                                                
     በሌላ መኪና የተሳፈረች አንድ ሌላ ህጻንም እንዲሁ አየር አጥሯት ስትደክም ፣ ሾፌሩ አቁሞ ህክምና እንድታገኝ አድርጓል አካባቢውን እንዲለቁ ከተጠየቁት መካከል ሁለት ሰዎች ታርደው መገኘታቸውን ግለሰቡ ገልጸዋል።
     ከሁለት ቀን በፊት በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ 60 የአማራ ተወላጆችን  ይዞ ሲጓዝ የነበረ አይሱዙ መኪና ተገልብጦ 59 ሰዎች መሞታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የአማራ ክልል ተወካዮች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረግ መጀመራቸውንም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ሰው ገልጸዋል።

ጋዜጠኛ እስክንድርና አቶ አንዱለአም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

     መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም  ኢሳት ዜና:-ቃሊቲ ማረሚያ ቤት፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አቶ አንዱአለም አራጌን ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ቀርቷል። የፍርድ ቤቱ ፖሊስ ለእስር ቤቱ ሀላፊዎች ደብዳቤ ማድረሷን ገልጻለች።
     የፌደራል ጠ/ፍርድ ቤት በ አቶ አንዱ አለም አራጌ የክስ መዝገብ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ወንጀል የተፈረደባቸውን የ አንድነት ፓርቲ ም/ል ሊ/መንበር እና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አንዱአለም አራጌ ፣ የአንድነት አመራር አባል ናትናኤል መኮንን፣  ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣  የቀድሞው የፓርላማ ተማራጭ አቶ አንዱአለም አያሌው ፣ የመኢዴፓ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ፣ አቶ ዮናስ ተረፈ፣ እና ሻምበል የሽዋስ ይሁን አለም የይግባኝ አቤቱታ በአግባቡ አለመመርመሩን ገልጿል።
     የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለማድመጥ የተከሳሽ ቤተሰቦች ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በርካታ ወጣቶች የተገኙ ቢሆንም ፣ ዳኛው አቃቢ ህጉንና የተከሳሽ ጠበቆችን ጠርተው በማነጋገር ጥቂት ጋዜጠኞች ብቻ ችሎቱን መታዘብ እንዲችሉ አድርገዋል።
     በእለቱ ችሎት የተሰየሙት ዳኛ አቶ ዳኘ መላኩ ብቻ የነበሩ ሲሆን የእስረኞች ጠበቃ አቶ ደርበው ተመስገን ፣ አቶ አበበ ጉታ እና የመንግስት ጠበቃ አቶ ሳሙኤል አባተም ተገኝተዋል። ዳኛው ዳኘ መላኩም ለጠበቆች “እናንተ ምንም የምታምኑት ነገር የለም፣ አቃቢ ህግ ያለምንም የሰው  እና የሰነድ ማስረጃ  ክስ ስላቀረበ ብቻ ነው የተፈረደባቸው ፣ እኛ በ አግባቡ ተከላክለን እያለ ነው የተፈረደባቸው ስላላችሁ መዝገቡን በአግባቡ ሀ ብለን እየመረመርን ነው፣ በዚህም ላይ የፌደራል ፍርድ ቤት መዝገቡን አዘግይቶ ነው የላከልን ስለዚህ ለእናንተም በአግባቡ ቢመረመር ጥሩ ነው” በማለት ተናግረው፣ እስር ቤቱ እስረኞችን ለምን እንዳላቀረባቸው የእስር ቤቱን ፖሊስ አዛዥም እንጠይቃለን ብለዋል።
     አንዲት ፖሊስ  ቀርባ  ” እኔ የማቅረቢያ የጥሪ ወረቀቱን ለማረሚያ ቤቱ ጸሀፊዎች በአግባቡ ሰጥቻለሁ ለምን እንዲቀርቡ እንዳላደረጉ  አልገባኝም፣ ወረቀቱ አልደረሰንም በማለት ሸምጥጠው ክደዋል፣ በማረሚያ ቤቱ እንዲህ አይነት መካካድ ያለ ነው ” በማለት ተናግራ ፣ ዛሬ የመጣሁት ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ለመውሰድ ነው ብላለች።
     ፍርድቤቱም ተከሳሾች ባልቀረቡበት ችሎት ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ዓም የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
     ችሎቱ ከተበተነ በሁዋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፖሊሶች እነ አቶ ናትናኤል መኮንንን፣ አንዱአልም አያሌውን፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበን ፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈንና፣ ሻምበል የሽዋስ ይሁን አለምን ይዘው የመጡ ሲሆን፣ ቢሆንም ወዲያው መልሰው ወደ እስር ቤት ወስደዋቸዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና አቶ አንዱአለም አራጌን ግን  ማረሚያ ቤቱ ፍርድ ቤት ሳያቀርባቸው ቀርቷል።
     ጠበቆች ለኢሳት እንደገለጡት እስረኞች ምንም አይነት የሽብርተኝነት ወንጀል ያልሰሩ መሆናቸው እየታወቀ መንግስት ስለከሰሳቸው ብቻ ወንጀለኞች ተብለው በግፍ ለእስር ተዳርገዋል።

 አቶ አዲሱ ለገሰ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን በሀሜተኝነት ነቀፉ፤ አስጠነቀቁም

     መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና:- “ስለዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ስናወራ በአስተሳሰብም በተግባርም ወደ አንድ መምጣት መቻል አለብን። አሁን ባለው አቀራረብ ከሄድን ግን መቀራረቡ አይደለም የሚጨምረው”ሲሉ አቶ አዲሱ ለገሰ  የ ኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን አስጠነቀቁ።
     የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራር የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ አባል ድርጅቶቹን ያስጠነቀቁት “መተካካቱ በብአዴን ውስጥ በተቀመጠው እቅድ አልተተገበረም” በማለት  እርሳቸውና ድርጅታቸው በሌሎቹ ድርጅቶች አመራሮች በመታማታቸው ነው።
     ሰንደቅ እንደዘገበው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰሞኑን በተናጠል ባካሄዱት ጉባዔ ነባር አመራሮችን ወደማዕከላዊ ኮሚቴ መልሶ የመምረጥ ሁኔታ መታየቱ ከመተካካት መርህ አንጻር በግንባሩ አባላት ሳይቀር ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።
     ህወሃት አቶ አባይ ጸሐዬን፣ ብአዴን እነአቶ አዲሱ ለገሰን እና አቶ ህላዊ ዮሴፍን በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የመረጡ ሲሆን፤ ሌሎችም በአዲስ መተካት ያለባቸው ነባር አባላት በአመራርነት መቀጠላቸው ጥያቄ አጭሯል።
     ሰሞኑን በባህርዳር በተካሄደው ጉባኤ ላይ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ እና ጥያቄ ሲያስነሳ የሰነበተው  የመተካካት ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንኑ አስመልክተው ነው አቶ አዲሱ ማብራሪያ እና ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት።  
     “ብአዴን የአመራር መተካካትን በተገቢው መንገድ አልፈጸመም “በሚል የተነገሩ ሐሜቶች መሠረተቢስ ናቸው” ያሉት አቶ አዲሱ “ ሁኔታውም በአመለካከት ደረጃ ለግንባሩ አይጠቅምም” ብለዋል።
     “ስለመተካካት ስናነሳ ማነው፤ ማንን የሚተካው የሚለው መታየት አለበት” ያሉት አቶ አዲሱ አንዳንዴ በትግሉ ጊዜ  አመራር የነበሩትን መተካት ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
     አያይዘውም “እንደሰማሁት ብአዴን መተካካቱን በደንብ አልሄደበትም የሚል ሃሜት አለ። ግን ይሄ አይጠቅምም። አንዱ ለግንባራችን አደጋ የሚመስለኝ ፣ በግሌም የሚሰማኝና ወደፊትም መታየት አለበት ብዬ የማምነው፤ አንዱ ድርጅት ውስጥ ጉድለት እንኳን ቢኖር ጉድለቱ እንዲታረም እንደታጋይ መታገል ተገቢ ነው። የአንዱ ጉድለት ለሌላው ጥንካሬ ሊሆን አይችልም። የአንዱ ጥንካሬ ለሌላው ድርጅት ግን ጥንካሬ ሊሆን ይችላል። በስልጠናም ብዙ ጊዜ ያየነው ይህን ነው። አንድ ድርጅት ሲደክም ለምን ደከመ? አንድ አካሌ ነው የደከመው? ይህ አካሌ ደግሞ በዛው ከቀጠለ እንደኢሕአዴግ እደክማለሁ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።”ብለዋል አቶ አዲሱ።
     የብአዴኑ አቶ አዲሱ አክለውም፦” በፍጥነትም ለማደግ የሚቻለው፤ የአንዱ መድክም የእኔም መድከም ነው የሚል አመለካከት ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ጨፍልቆ አንድ ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። ስለዴሞክራሲያዊ ድርጅትም ስናወራ፤ በአስተሳሰብም፣ በተግባርም ወደ አንድ መምጣት መቻል አለብን። አሁን ባለው አቀራረብ ከሄድን ግን ፤መቀራረቡ አይደለም የሚጨምረው” በማለት መለያየት ሊኖርም እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ የማስጠንቀቂያ ደወል አሰምተዋል።
     እንደ ሰንደቅ ዘገባ፤አቶ ሕላዊ ዮሴፍም በጉባኤው ውስጥ ስለሚወራው ሃሜት ጥያቄ በማቅረብ ነበር ሃሳባቸውን ያቀረቡት።
     “የመተካካት መሠረታዊ ጭብጥ የተጀመረውን መስመር ማስቀጠል መሆኑን ግንዛቤ ከወሰድን፤ የግለሰቦችን ጉዳይ በአጀንዳነት ማንሳቱ ለምን አስፈለገ? ምንስ ይጠቅማል? ድርጅታችንን እየጎዳው ያለው ነገር ምንድን ነው? የሚሉትን ትንሽ ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገሩ የሚጠቅም ይመስለኛል።”፡ያሉት አቶ ሀላዊ፤” ድርጅታችን ወደፊት ማራመድ በሚቻልበት አግባብ ላይ እርግጠኛ ምላሽ በምናገኝበት ሁኔታ ተግባብተን መውጣት አለብን። አለበለዚያ በነገሮች ሁሉ ፊት ለፊት ሳንተያይ በጎን እየተላለፍን ሊሆን ይችላል።”ብለዋል።
     አቶ ህላዊ አክለውም፦”በተረፈ ሁሉም በየድርጅቱ የነበረው ሂደት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ። የእኛም ሁኔታ በበቂ መረጃ የቀረበ ነው። ከስልሳ አምስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ውስጥ ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆኑት አዲስ ተተኪዎች ናቸው። ይህ ሆኖ ሳለ፤ በሁለት ሰዎች ላይ እናተኩር፣ አይናችንን ጥለን እንሂድ የሚባል ከሆነ ፤ልማቱን አላራምድ ያለ አደርባይነት እዚህ ቦታ እንዴት ይገለፃል ብለን ብናየው ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉ ሀሜት አምተዋል  ተብለው ሚጠበቁትን ያስደነገጠ ንግግር አድርገዋል።
     አቶ አዲሱ ለገሰንና አቶ ህላዊ ዮሴፍን ጨምሮ ነባር የኢህአዴግ አመራሮች በአዲሱ ስራ አስፈፃሚ ወስጥ መካተታቸወ፡ይታወቃል :፡
     በተለይ አቶ አዲሱ ለገሰ -ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ባስተዋወቁበት ወቅት በመተካካቱ መመሪያ  ከፖለቲካው እንዳረፉና በአማካሪነት እንደሚያገለግሉ ቃል ከገቡ በሁዋላ፤ አቶ መለስ ማረፋቸውን ተከትሎ  በአዲሱ የብአዴን አመራር ውስጥ መካተታቸው ብዙዎችን አነጋግሯል።“በአሁን ሰዓት ስለመተካካት የሚወራው ማዕከላዊ ላይ ምን ተደረገ? ስራአስፈፃሚው ላይ ምን ለውጥ አለ? የሚሉ ናቸው።” በማለት ሀሳባቸውን መስጠት የጀመሩት የህወሀቱ አቶ አባይ ፀሀዬ በበኩላቸው፤” ቁምነገሩ ያለው መካከለኛው አመራር ላይ በጥራትና በስፋት የሚተካ አመራር መፍጠር ላይ ነው። ይህ ሲሆን ማዕከላዊ ኮሚቴውንም፣ ሌላውንም ለመተካት ብዙ አማራጭ ይኖራል። ስለዚህ የመተካካት ሂደቱን ስንገመግም ከበላይ ያለውን አመራር ብቻ መሆን የለበትም። “ብለዋ
     “የመተካካት ፖሊሲዎቻችን ምንድናቸው?” በሚል ጥያቄ አስተያየት መስጠት የጀመረት አተ በረከት ሰምዖን በበኩላቸው ፤ እኔ እንደሚገባኝ፣ መተካካት የሚባለው ለትግል ቀጣይነት፣  የሚደረግ ሂደት ነው። የመተካካት ግቡ የሰዎች መተካካት አይደለም። ግቡ የመስመር ትግበራ ነው። “ብለዋል።
     አክለውም፦“ነባሮች በጣም ከመድከማቸው በፊት በተለይ ከፊት መስመር ቦታውን ለወጣቱ ትውልድ ማስረከብ አለባቸው፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የተረከበውን መስመር በዲሲፕሊን በታማኝነት በፅናት ተግባራዊ በማድረግ መቀጠል አለበት። ነባሩም ከፊት መስመር በመውጣት በጎን ማገዝ ይጠበቅበታል። ሌላው፤ በመንግስት ኃላፊነት ነባሩም ሆነ ተተኪው ከሁለት የምርጫ ጊዜ በላይ አያገለግልም። በፓርቲ ኃላፊነት ውስጥም አንድ ሰው እስከ ስልሳ አምስት ዓመት ብቻ ነው የሚያገለግለው። የፓርቲያችን የመተካካት ፖሊሲዎችም ዋነኛ ቁምነገሮች እኔ እስከማስታውሰው ድረስ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ናቸው።”ብለዋል።
     ጋዜጣው እንዳለው በጉባኤው ላይ የተንፀባረቀው የመተካካት አተገባበር ወጥነት የሌለው እና ድርጅቶቹ በተናጠል የሄዱበት በመሆኑ፤ ግንባሩ የአፈፃፀም የፖሊሲ አቅጣጫ እንጂ የአተገባበር ዝርዝር መመሪያዎች የሌሉት በመሆኑ በጉባኤው ተሳታፊው አባላት ውስጥ የመተካካቱ ሂደት ለሃሜት የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
     “ ሌላው ተተኪ ከሚባለው አዲሱ አመራርም መተካካቱን በተመለከተ ከፍተኛ ሙግት ያንፀባረቀ አልነበረም ያለው “ጋዜጣው፤” በአብዛኛው የቀድሞ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች ተሳትፎ የጎላበት ጉባኤ ነበር ማለት ይቻላል” ብሏል።

ኢህአዴግ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ

     መጋቢት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም  ኢሳት ዜና:-በባህርዳር የተካሄደው 9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝን ድርጅቱን በሚቀጥሉት 5 አመታት እንዲመሩ መርጧቸዋል። የብአዴኑ ሊቀመንበርና የትምህርት ሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
     ኢህአዴግ በዚህ ጉባኤ የአመራር ችግር እንደገጠመው በተለይም አመራሩና አባላቱ ተነሳሽነታቸው መቀነሱን ይፋ አድርጓል። ትግሉን ወደፊት ለማስቀጠለም አባላቱና አመራሩ የተከፈለውን መስዋትነት ልብ ሊሉት እንደሚገባ መክሯል። በአገሪቱ ውስጥ የመልካም አስተዳዳር እጦት መስፈኑንና የ5 አመቱን የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማስቀጠል የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመው ጉባኤው መተማመን ላይ ደርሷል።
     በተያያዘ ዜናም ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ከኢህአዴግ አመራርነት ተሰናብተዋል።
    በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳዳር የሆኑት ወ/ሮ ገነት ዘውዴ በእድሜ መግፋት በሚል ምክንያት ከኢህአዴግ አመራርነት በዛሬው እለት በይፋ ተገለዋል። ወ/ሮ ገነት የተገለሉት የኢህአዴግ አማራሮች እድሜ እድሜ ከ65 በላይ መሆን የለበትም በሚለው መርህ መሰረት ነው ተብሎአል።
    ወ/ሮ ገነት በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ጥራት እንዲወድቅ በማድረግ ፣ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የጸጥታ ሀይሎች እርምጃዎች ሲወስዱ ለማስቆም ባለመቻላቸው ይተቻሉ።
     በኢህአዴግ መመሪያ መሰረት 65 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ጡረታ ይወጣል፡፡አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ መመሪያው በአቶ በረከት ይፋ ሲደረግ እነሱ ሲያረጁ ነው ወይ የዚህ ዓይነት መመሪያ የሚያወጡት የሚል ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡ 

የእስልምና ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ግለሰብ ብአዴን ኮትኩቶ ያሳደጋቸው ሰው መሆናቸው ታወቀ 

     መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና:-በቅርቡ ከተካሄደው ምርጫ በፊት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ሀጂ መሁመድ ሲራጅ ሙሀመድ ኑር አባታቸው ዋግ ውስጥ ነባር የብአዴን ታጋይ የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ተፈራ ዋልዋ እና የአቶ አዲሱ ለገሰ የቅርብ ሰው እንደነበሩ ከብአዴን ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
     ግለሰቡ በአወልያ የተጀመረው ተቃውሞ እንዲኮላሽ ከመንግስት ከፍተኛ ተልእኮ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩና አሁንም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋም ለመንግስት ምክር እየሰጡ የሚገኙ ናቸው።
     የግለሰቡ ታሪክ እንደሚያስረዳው ታጋይ አባታቸው ሲራህ መሀመድ ኑር እንደሞቱ ወጣቱ ሲራጅ በአቶ አዲሱ አማካኝት የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበርን እንዲያደራጁ ተመርጠው ማህበሩ እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በዚህ አስተዋጽኦቸውም፣ ምንም አይነት በቂ የእስልምና እምነት ትምህርት ሳይኖራቸው የአማራ ክልል እስልምና ጉባኤ ሃላፊ ተብለው በመንግስት ከተሾሙ በሁዋላ ለተወሰነ ጊዜ በክልሉ ውስጥ እንቅስቃሴ አድርገዋል።     በ1997 ዓም ግለሰቡ ወደ ፌደራል ተዛውረው መጠነኛ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርት እንዲቀስሙ ከተደረጉ በሁዋላ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ በመሆን ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
     ሀጂ ሙሀመድ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የክልሉን የእስልምና ምክር ቤት በከተማዋ መሀል አደባባይ ላይ በአለ አራት ፎቅ ህንጻ እያሰሩ ሳለ፣ ከህንጻው ስራ ጋር በተያያዘ ገንዘብ ማጉደላቸው በመረጋገጡ ፣ የህንጻው ስራ እስካሁን ካለመጠናቀቁም በላይ ግለሰቡ እንዳይጠየቁ ተደርጓል።
     በሰቆጣ ለእናታቸው እጅግ ዘመናዊ ህንጻ የገነቡት ሀጂ ሙሀመድ፣ ሶስት የንግድ መኪኖችን ገዝተው በንግድ ስራ ላይ ከመሰማራታቸው በላይ፣ በባህርዳር፣ በአዲስ አበባ እና በሰቆጣ የንግድ ቤቶችንና የመኖሪያ ቤቶችን በራሳቸውና በወንድሞቻቸው ስም በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ወደ ሀብታሞች ጎራ ለመቀላቀል ችለዋል።
     በቅርቡ በተደረገው የመጅሊስ ምርጫ ስልጣናቸውን ያስረከቡት የ40 አመቱ ሀጂ ሙሀመድ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልማት ኤጀንሲ የተባለ ድርጅት ከፍተው መንግስትን እያማከሩ ነው።
     በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊም መሪዎች እና ድምጻችን ይሰማ በማለት ዘወትር አርብ ተቃውሞ የሚያሰሙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ምክር ቤቱ ነጻ አይደለም በማለት ጥያቄ ማቅረባቸው ትክክልና በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን የብአዴን ምንጮች የዋና ጸሀፊውን ማንነት በማስረጃ በማስደፍ እንደ ማሳያ አቅርበዋል። በቅርቡ የተተኩት የመጅሊስ አባላትም እንዲሁ የኢህአዴግ ቀንደኛ ደጋፊና አባላት መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አያይዞ ገልጾአል።
     አቶ ተፈራ ዋልዋ ብዙውን ጊዜ አቶ አዲሱ ለገሰ ደግሞ አልፎ አልፎ በህይወት ያሉት የሀጅ መሀመድ ሲራጅን እናት የታጋይ ሲራጅ ሙሀመድ ኑርን ባለቤት እየሄዱ እንደሚጠየቁቸው ታውቋል።
     በጉዳዩ ዙሪያ የሀጂ አል ሙሀመድ ሲራጅን አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu