Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Breaking News

ከዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሳውዲ ዐረቢያ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

Published Posted on by | By TZTA News

ከዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሳውዲ ዐረቢያ  የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


ጥቅምት 27 ቀን 2006

በቅርቡ በሳውዲ ዐረቢያ በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተነዘረው ጥቃት፣ እንግልት፣ ግድያና በእህቶቻችን ላይ የደረሱ ቡድናዊ አስገድዶ መድፈር በታሪካችን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ብሔራዊ ውርደት አድርገን እንድንወስደው ሁኔታው አስገድዶናል፡፡

ይህ አሳዛኝ ዜና እንደተሰማ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየአደባባዩ በሳውዲና በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በመሰለፍ ቁጣቸውን ማሰማታቸውና የዓለም አቀፍ መንግስታትና ሰብዓዊ ድርጅቶችን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ከምንም ጊዜ በላይ ጎልቶ የታየ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ለዚህ ዓለም አቀፍ ትብብር መፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ይህ ህዝባዊ መነሳሳት የፖለቲካ፣ የዘር፣ የሀይማኖት ልዩነት ያልታየበት ሁሉን አቀፍ መሆኑ ለስኬታማነቱ ትልቅ አስተዋጽኦ
አበርክቷል። ይበልጥ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ እንዲቀጥልም ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ
አውስትራሊያ፣ ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት ያሳዩት የጋራ ቁጣና እንቅስቃሴ ወገኖቻችንን ለመታደግ የሚያስችል ውጤት እንዲያስገኝ ትብብሩ ዕቅድና ስልት አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ትላንትና በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ስላለው በደል ሲጠየቅ “ጥቂቶች ናቸው፡፡ የሳውዲ መንግስት የሚወስደው እርምጃ በህገ ወጥ ሠራተኞች ላይ እስከሆነ ጊዜ ድረስ የሉዓላዊነት መብቱ ነው ወዘተ” እያለ ሲዘባበትብን የነበረውን አምባገነንና ‹‹የዘመናዊ ባሪያ ፈንጋይ ስርዓት›› አፍንጫውን ሰንጎ በመያዝ የወገኖቻችንን ጩኸት እንዲያዳምጥ ብቻ ሳይሆን በአገር ቤትም ህዝባዊ ቁጣን በመቀስቀሱ የአዞ እንባ እንዲያነባና ‹‹አኬልዳማ ቁጥር 2›› ድራማ በአዳዲስ ተዋናዮች እንዲሰራ ያስገደደውን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በሳውዲ ዐረቢያ›› በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ዕውቀትና ተመክሮ ያላቸው አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሀይማኖት መሪዎችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችን በማሰባሰብ ወገኖቻችንን የመታደግ የጋራ ዓላማ አንግቦ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ዓለም አቀፍ ዋና ዋና የዜና መገናኛዎች ዜናውን እንዲዘግቡ ለማድረግ የተለያዩ ቃለ መጠይቆችን በማዘጋጀት መግለጫዎች እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተደርጓል፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብሩ በተለያዩ አገራትና ከተሞች በዚህ ችግር ላይ ለማተኮር ከተሰባሰቡ ወገኖች ጋር የተቀናበረ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ መረብ በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከዳር እስከ ዳር በቁጣ የተነሳሳው ኢትዮጵያዊ “ምን እናድርግ፣ በገንዘብ እንርዳ፣ ለወገኖቻችን በፍጥነት እንድረስ ወዘተ” የሚል ከፍተኛ ግፊት እያደረገ ሲሆን ለዚህ ሁሉ ሰቆቃና ብሔራዊ ውርደት የዳረገን አምባገነናዊ ስርዓት ጭራሽ ዓይኑን በጨው አጥቦ የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ለማስመሰል የጀመረውን ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና የቁራ ጨኸት፤ ጥቃት የደረሰባቸውን በሚታደግ ተጨባጭ እንቅስቃሴ መቋቋም ፋታ የማይሰጠው አንገብጋቢ እርምጃ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሆኑም፣ በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ቀጣፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጆሮ ሳትሰጡ ባለመዘናጋት እንቅስቃሴውን የበለጠ እንድታቀጣጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ሁኔታዎች እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ እየተለዋወጡ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት ቀልጣፋና ወሳኝ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት መልክ መደራጀት አማራጭ የሌለው በመሆኑ የዓለም አቀፍ ትብብሩ የጋራ አመራር አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ሁኔታዎችን በጥልቀትና በስፋት ከገመገመ በኋላ ሁሉን በሚያሳትፍ መልኩ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሚያንፀባርቅ አደረጃጀት እንዲፈጠር ወስኗል።

በዚህ መሠረት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን የሚመራና የሚያስተባብር በቂ የሰው ሀይል የተመደበለት አንድ ጊዜያዊ የማስተባበሪያ ጽ/ቤት በዋሽንግተን ዲሲ መቋቋሙን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው፡፡ በተጨማሪም የዕርዳታ ማስተባበሪያ፣ የውጭ ግንኙነትና የሕጋዊ እርምጃ ግብረ ኃይላት ተቋቁመው አግባብ ካላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ ጀምረዋል።

ስለሆነም በመላው ዓለም በየአካባቢው የተሰባሰባችሁ ወገኖች በዚህ እንቅስቃሴ ከጽ/ቤቱ ጋር በአስቸኳይ ግንኙነት እየፈጠራችሁ እንቅስቃሴውን በበለጠ እንድታቀጣጥሉት ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የትብብሩ አሠራር ግልፅ፣ አስተማማኝና ተጠያቂነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንዲቻል፤ የሒሳብ፣ የኦዲት፣ የሕዝብ ግንኙነትና የጠቅላላ አገልግሎት ክፍሎች ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ተሟልተው እንዲደራጁ ተደርጓል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አዲስ ድረ-ገጽ መቋቋሙን እያበሰርን አዲሱ የባንክ አካውንት ቁጥር፣ የጽ/ቤቱ ስልክና አድራሻ ከታች
የተዘረዘረው መሆኑን እንገልፃለን፡፡

በመጨረሻም ትብብሩ በአፋጣኝ መፈጸም አለበት ብሎ የተስማማበትን መርሀ ግብር ከዚህ በታች የተጠቀሱትን የሚያጠቃልል ስለሆነ፤ ሁላችንም በነዚህ ተግባራት ክንውን ላይ አተኩረን ለስኬታማነታቸው የየበኩላችንን ያልተቆጠበ አስተዋፅዖ እንድናደርግ በአጽንዖት እናሳስባለን።
እነዚህም፡-
1ኛ- በሳውዲ ዐረቢያና በየመን የሚገኙት ወኞቻችንን ጎብኝቶ መረጃ የሚያሰባስብና ዕርዳታ የሚያደርሱበትን ሁኔታ የሚያመቻች የልዑካን ቡድን በአፋጣኝ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ፣

2ኛ- አስተማማኝ ከሆኑ ዓለም አቀፍ የግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚገኘው ዕርዳታ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች በአፋጣኝ እንዲደርስ ማድረግ፣

3ኛ- በሚቀጥለው ዓርብ ጥቅምት 27 ቀን (ዲሴምበር 6) በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች በወገኞቻችን ላይ የደረሰውን ግድያና እንግልት በማሰብ የፀሎት ስነ ስርዓት እንዲደረግና በወቅቱም ዕርዳታ እንዲሰባሰብ ጥሪ
ማቅረብ፣

4ኛ- እሁድ ጥቅምት 29 ቀን (ዲሴምበር 8) የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች በየቤተክርስቲያኑ የሀዘን ቀንና የፀሎት ስነ ስርዓት በማካሄድና ዕርዳታ በማሰባሰብ ወገኖቻቸውን እንዲታደጉ ጥሪ ማቅረብ፣

5ኛ- የሀይማኖት መሪዎች በየአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አንድነት በማጠናከር የተለመደውን ወገናዊ ምላሽ እንዲሰጡ ማሳሰብ፣

6ኛ- በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማክሰኞ ታኅሣስ 1 ቀን (ዲሴምበር 10) የአንድ ቀን የረሃብ አድማ በማድረግ
የወኞቻችንን ሰቆቃ እንደምንሳተፍ በተግባር እንዲያሳዩና ለምግብ ይውል የነበረውን ለወገኖቻችን መርጃ እንዲሰጥ ማድረግ፣

7ኛ- በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው እየተሰባሰቡ ከትብብሩ ጋር በማበር ለወገን ደራሽነታቸውን
በተግባር ለማስመስከር የጀመሩትን እንቅስቃሴ አፋፍመው እንዲቀጥሉ ማስተባበር፣

8ኛ- በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአፍሪካ-አሜሪካን የኮንግረስ አባላት በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የዘር
መድሎ የተላበሰ መሆኑን ተረድተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ መጎትጎት፣
ከዚህም ጋር በተጨማሪ በየቦታው የሻማ ማብራት ሥነ ስርዓት በማድረግ ለወገኞቻችን በአስቸኳይ ሊደርስ የሚገባውን እርዳታ የማሰባሰብ ተግባር በስፋት እንዲካሄድ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ በወገኖቻች ላይ የደረሰው ግድያና በደል ፍትህ እስኪያገኝ ትግላችን ይቀጥላል፡፡

የወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ድረ-ገፅ፡ www.defendethiopians.org
ኢ-ሜይል፡ info@defendethiopians.org
ስልክ ቁጥር፡ (877) RING-ETHIOPIA / 1 (877) 746-4384
የባንክ ሒሳብ፡-
Bank Name: Chase Bank
Account Name: ENPCP-GAFRESA
Account Number: 994431476
Routing Number: 072000326
Swift Code: CHASUS33
Bank Address: Frandor Branch-197
3118 East Saginaw St.
Lansing, MI 48912
U.S.A.

Global Alliance for the Rights of Ethiopians and mail to:
c/o ESAT USA
P.O. Box 11261
Alexandria, VA 22312


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu