Logo

Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
ad ad ad ad ad

Amharic News, Breaking News Amharic, Ethiopian

40 – 23 የኢህአዴግ የጎሳና የመጥበብ ሰረገላ ሐዲዱ ላይ ነውን? “ኢትዮጵያን በጎሳ ሳጥን ቆልፎ የሚጓዘው ህወሃትና ድግሱ”

Published Posted on by | By TZTA News

40 – 23 የኢህአዴግ የጎሳና የመጥበብ ሰረገላ ሐዲዱ ላይ ነውን? “ኢትዮጵያን በጎሳ ሳጥን ቆልፎ የሚጓዘው ህወሃትና ድግሱ”

Spread the love

ህወሃት በነጻ አውጪ ስም ታግሎ ኢትዮጵያን መግዛት የጀመረበትን 23ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው። ወዳጆቹና መሪዎቹ ባስቀመጡት እቅድ መሰረት ኢትዮጵያን “በመተካካትና በተሃድሶ” ስም ራሱን እያገላበጠ ለመግዛት የቆረጠው ጊዜ በትንሹ 40 ዓመታት እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ባለው የሰረገላው ጉዞ ኢህአዴግ ከ40 – 23 ከመቀነሱ ውጪ አሰበበት ስለመድረሱ መገመት የሚያስችል ምልክት የለም። እንደውም ስጋት እንጂ።

ሲጀመር “የገበሬ ተሟጋች” ነኝ በማለት ራሱን የአርሶ አደሩ ወኪል አድርጎ የተነሳው ህወሃት፣ ኢህአዴግ ሆኖ አገር መግዛት ሲጀምር ያስቀደመው የብሄር ብሄረሰቦችን የመብት ጥያቄ እንደ ውዳሴ ጸሎት በመደጋገም ነበር። በዚሁ በጎሳ ላይ ተመስርቶ በቋንቋ የተቆለፈው የአገዛዝ ስልት ሲጀመር ማስጠንቀቂያ የሰጡ፣ ለመታገል የሞከሩ፣ የታገሉ፣ ያስተባበሩ፣ ያደራጁ የህወሃት የ40 ዓመት ጉዞ ጸር ተደርገው ተወሰዱ። ስለ ኢትዮጵያ ጥቅምና ኢትዮጵያዊነት ያሳሰቡ ጠላት ተደርገው ተፈረጁ። በስውር በአፈና፣ በግልጽ ህግ እየተጠቀሰባቸው ከጫወታና ከመኖር ተገለሉ። ብዙዎች እንደሚሉት “የጉዳቱን መጠን ህወሃትና የተጎዱት ቤተሰቦች ይቁጠሩት”!

ግንቦት ሃያ “የህዝብ የድል ክቡር ቀን ነው” በሚሉና “የህዝብና የአገር ውድቀት የታወጀበት የክፉ ቀኖች ሁሉ ድምር” ሲሉ በሚሰይሙት መካከል ሰፊ መከራከሪያ አለ። የመንገድ ግንባታ፣ የህንጻ ግንባታ፣ የኮሌጅና የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የግድቦች ግንባታና የአባይ ወንዝ ልማት ወዘተ ጉዳዮች የግንቦት 20 ጣፋጭ ፍሬዎች ስለመሆናቸው “የቀኑ ወዳጆች” ይከራከራሉ። የቀኑ “ባሮችም” ይህንኑ ውዳሴ በማቀንቀን ታማኝነታቸውን ይገልጻሉ። በጥቅም የተደለሉ ሎሌዎች ስለሆኑ ይህንን ድል ለማስጠበቅ በግልጽና በህቡዕ አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ።

በተጠቀሱት የልማት ስራዎች ላይ ተቃውሞ የማያነሱ የቀኑ “ሰለባዎች” ሰላምና መረጋጋት እንዳለ የሚሰብክ አስተዳደር ልማትን ከመስራት ሌላ ተግባር እንደሌለው ይገልጻሉ። አያይዘውም ጣሊያንም በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ መንገድና ድልድዮችን መገንባቱን ያጣቅሳሉ። ከሁሉም በላይ ግን ኢህአዴግ በሚገዛት አገርና ሕዝብ ስም የተበደረውን የገንዘብ መጠን “ከተዘረፈው ውጪ” በማለት ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ “መንገድ መስራትና ህንጻ ማቆም የመብት ጥያቄን በጥይት ለመመለስና በደም ለመጨማለቅ ዋስትና ሊሆን አይችልም” በማለት ስርዓቱን አጥብቀው ይኮንኑታል።

በሌላም ወገን የተሰሩትን ህንጻዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ የገንዘብ ተቋማት፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች በማንሳት “የግንቦት 20 ፍሬዎች” ሲሉ ይሰይሟቸዋል። ሲያብራሩም “የነዚህ ሁሉ ሃብቶች መነሻና ባለቤቶች ህወሃትና ህወሃት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ባለሟሎች ናቸው። የህዝብ አይደሉም። ሕዝብም አያምንባቸውም” በማለት ጥርስ ይነክሱባቸዋል። በዝርፊያ ሃብት የሚያግበሰብሰውን ኤፈርት ኢትዮጵያን “ንብረቶችሽን ባደራ ላስቀምጥ” የሚል እስከሚመስል የንግድ ኢምፓየሩን ማስፋቱን አብዝተው ይኮንናሉ።

የግንቦት 20፣ የቀኑ ወዳጆች ኤፈርት ላይ የሚቀርበውን ጥያቄ አያስተባብሉትም። ይልቁኑም ድርጅቱ ጓዳና ካዝናው የተለጎመ መሆኑ ያብከነክናቸዋል። አለው የሚባለው ሃብት ሁሉ የትኛው ቋት እንደሚቀበር ስለማይረዱ “የተሸውደናል” ስሜት አላቸው። ለዚህም ይመስላል የህወሃት ወዳጆች “ኤፈርትን ያየህ ወዲህ በለኝ” ሲሉ የሚደመጡት። በግልጽ አነጋገር ኤፈርት ፊት ለፊት ከሚያሳየው ሃብቱ ይልቅ፣ የማይታው ጉዱ ስለሚያመዝን በህወሃት ወዳጆች ሳይቀር አልሞ ተኳሽ (ስናይፐር) የተደቀነበት ነው።

አፈናው፣ ግድያው፣ እስሩ፣ ዝርፊያው፣ ከላይ ከተገለጸው በተቃራኒ አርሶ አደሩ ላይ የሚፈጸመው የመሬት ቅሚያ ሌላው የግንቦት 20 የጨነገፈ ፍሬ ተደርጎ ይወሰዳል የሚሉ አሉ። በተለይም ራሱ ህወሃት ሁሉንም በራሱ ደረጃ ለማሳነስ ሲል ያዋቀረው የቋንቋና ጎሳን ተገን ያደረገ የአገዛዝ ስልት ዛሬ ግንቦት 20ን እድሜውን ወደ ማሳጠር እያደረሱት ነው ሲሉ ያክላሉ። በዚህ አስተሳሰብ ላይ የሚተቹ ሰሞኑን አጠንክረው እንደገለጸት “የግንቦት 20 ወዳጆች ኢትዮጵያዊነት ከውስጣቸው እንዲወልቅ ተደርጎ በተዘጋጀላቸው የትምህርት እቅድ፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ … መሰረት ወደ ጎሳ እየጠበቡ የግንቦት 20 ድል ‘ሰረገላው’ መድረስ የፈለገበት ቦታ ሳደርስ ሃዲዱን ሊያወላልቀው ይችላል”፡፡

40 – 23 ዓመት ላይ ያለው ኢህአዴግ ህወሃትን እያጀበና እየሞሸረ ወደ “መንገሻው” ለማድረስ የተሰሩበት የጎሳ ኬሚስትሪ እንደሚከለክላቸው የሚናገሩ ክፍሎች “የግንቦት 20 ድል እየተከበረ 40 ዓመት መዝለቅ ምናልባትም ከተረትም የወረደ ሟርት ነው” ባይ ናቸው። ህወሃት ለጊዜው ብሎ የዘራው የበቀል ዘርና በጎሳ ሳጥን ውስጥ ከቶ ያሳደጋቸው ወዳጆቹና በጊዜ የታሰረ ቦንብ እንደሚሆኑበት ምልክቶቹ ከበቂ በላይ እንደሆኑም ይናገራሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት “ህወሃትን የሚበሉት ራሱ ያመረታቸው ፈንጂዎቹ ናቸው” በመሆኑም የዘንድሮው ግንቦት 20 አንጸባራቂ ጥቅስ “ለመጥበብ ብሎ ህወሃት የወጠነው የጎሳ መዋቅርና አስተምህሮት የህወሃት ፉርጎ የሚሄድበትን ሃዲድ እያወላለቀው ነው” የሚለው ይሆናል – “ጉድጓድ የሚምስ ራሱ ይወቅድበታልና”፡፡

Source: http://www.goolgule.com/


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*

Comment validation by @

 
Logo
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu
Webmaster Savas Can Altun Teknoloji Bilgisayar Google s4v4s ASk Question Webmaster Sitesi Webmaster Forumu